የኢትዮጵያ ስካውት ማህበር ወጣቶች አለመግባባትና ልዩነቶችን በምክክር የመፍታት ልምድን ማዳበር እንዳለባቸው ገለጸ

160

ነሐሴ 06 ቀን 2014 (ኢዜአ) ወጣቶች አለመግባባትና ልዩነቶችን በምክክር የመፍታት ልምድን ሊያዳብሩ እንደሚገባ የኢትዮጵያ ስካውት ማህበር ገለጸ።

ማህበሩ ወጣቶች የምክክር ክህሎትን በማሳደግ በአገር ግንባታ ላይ የራሳቸውን ሚና እንዲወጡ የማስቻል ዓላማ ያለው "ምክክር ለሰላም" በሚል መሪ ሀሳብ ከመላው የአገሪቱ ክፍል ለተውጣጡ ስካውቶች እና ወጣቶች ለአራት ቀናት የሚቆይ ሥልጠና መስጠት ጀምሯል።

ወጣቶቹ ከስልጠናው የሚያገኙትን ልምድ በማካፈል የውይይትን አስፈላጊነት በሕብረተሰቡ ዘንድ የማስረጽ ሥራዎችን እንደሚያከናውኑ ተመላክቷል።

የኢትዮጵያ ስካውት ማህበር ዋና ኮሚሽነር ነብዩ መርዕድ እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት ውይይት ዋነኛው መሳሪያ ነው።

ወጣቶች ማንኛውንም አይነት ችግር ሰከን ብለው በማየት እራሳቸውን ከየትኛውም አይነት የጥፋት ተግባራት ሊያቅቡ ይገባል ብለዋል።

በውስጡ በርካታ ወጣቶችን የያዘው ማህበሩ የወጣቶች የውይይት ክህሎታት እንዲያድግ እየሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

የማህበሩ ምክትል ኮሚሽነር ማትያስ ሶማኖ በበኩላቸው፤ ሥልጠናው ወጣቶች የተለያዩ ችግሮች ሲፈጠሩ የመፍቻ መንገዶችን ለማሳየት ያለመ መሆኑን ገልጸዋል።

አለመግባባቶችን በሰላማዊ መንገድና በውይይት የመፍታት ዘዴ ወጣቶች ሊያዳብሩት የሚገባ ልምድ መሆን እንዳለበትም አስገንዝበዋል።

"ልዩነት ተፈጥሯዊ መሆኑን መገንዘብ ይገባል" ያለው ደግሞ የማህበሩ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ብሩክ መለሰ ነው።

እነዚህ ልዩነቶች ወደ ግጭት ሳይሄዱ ለምክክር ቅድሚያ በመስጠት በሰውና በንብረት ላይ ጉዳት እንዳይደርስ ማድረግ እንደሚገባ ገልጿል።

''በመወያየት እና በመነጋገር የማይፈቱ ችግሮች የሉም'' ያለው ወጣት ብሩክ፤ በየትኛውም አይነት ሁኔታ ደግሞ ደጋግሞ መወያየት ሊዳብር ይገባል ብሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም