የጤና መሠረተ ልማት ግንባታዎችን ተደራሽ ለማድረግ እየተሰራ ነው- ጤና ሚኒስቴር

141

ባህር ዳር፤ ነሐሴ 5/2014 (ኢዜአ)፡ በጤናው ዘርፍ ጥራታቸውን የጠበቁ የመሠረተ ልማት ግንባታዎችን በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች ተደራሽ ለማድረግ እየተሠራ መሆኑን የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የ2014 በጀት ዓመት የጤና መሠረተ ልማት ፕሮጀክቶች አፈፃፀም ግምገማና የ2015 በጀት ዓመት የዕቅድ ውይይት ፎረም ትናንት በባህር ዳር ተጀምሯል።

የጤና ሚኒስቴር ዴኤታ ዶክተር አየለ ተሾመ በመድረኩ ላይ እንዳሉት የጤና መሠረተ ልማት ስራዎችን በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች ፍትሃዊ በሆነ መልኩ ተደራሽ ለማድረግ በትኩረት እየተሠራ ነው።

ሚኒስቴሩ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት  ከጤና ኬላ እስከ መጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ደረጃቸውን የጠበቁ የጤና ተቋማትን  በሁሉም ክልሎች ገንብቶ ለአገልግሎት ማብቃቱን አስረድተዋል።

በተያዘው በጀት ዓመትም ቀደም ሲል ተጀምረው ያልተጠናቀቁን ማጠናቀቅና አዲስ የሚገነቡ መሠረተ ልማቶችን በመገንባትና በመጠገን ለህብረተሰቡ ጥራት ያለው የጤና አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።

በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የጤና መሰረተ ልማት ዳይሬክተር ኢንጅነር ታደሰ የማነ በበኩላቸው በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በፌዴራል መንግስት በ871 ሚሊዮን ብር ወጭ በግንባታ ላይ ከነበሩ 124 ፕሮጀክቶች 120ዎቹ ማጠናቀቅ ተችሏል።

በክልሎች ደግሞ በተለይ በገጠር የጤና አገልግሎትን ተደራሽ ለማድረግ ከተጀመሩት 1 ሺህ 500  የመሠረተ ልማት ፕሮጀክቶች  90 በመቶ የሚሆኑትን ማጠናቀቅ መቻሉን ገልጸዋል።

ከተጠናቀቁ ፕሮጀክቶች መካከልም በሁሉም ክልሎች የተገነቡ የ120 አዲስ የተገነቡ ጤና ኬላዎች፣ በታዳጊ ክልሎች ደግሞ 21 ጤና ጣቢያዎች ተጠናቀው ወደ ስራ መግባታቸውን ተናግረዋል።

የጤና ተቋማት ማስፋፊያና ጥገና፤ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ፣ የአካል ጉዳተኞች ማከሚያና የስልጠና ማዕከላት፣ የውሃና መብራት ማሟላት ስራዎች የመሠረተ ልማት ግንባታው አካል መሆናቸውን አመልክተዋል።

በያዝነው በጀት ዓመትም ከመንግስት፣ ከዓለም ባንክና ከሌሎች ረጂ ድርጅቶች በተገኘ 7 ቢሊዮን ብር በጀት 1 ሺህ 228 ፕሮጀክቶችን ለመገንባትና ለመጠገን ታቅዶ ወደ ተግባር መገባቱን አመልክተዋል።

ከነዚህ መካከልም 320ዎቹ በአማራና በአፋር ክልሎች በጦርነቱ የወደሙ ሆስፒታሎችና ሌሎች ጤና ተቋማት መሆናቸውን አስረድተዋል።

በጸጥታና በተለያዩ ምክንያቶች ለረጅም ጊዜ ቆመው የቆዩ ፕሮጀክቶችን በያዝነው በጀት ዓመት አጠናቆ ለአገልግሎት ለማብቃት ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከክልሎች ጋር ተቀራርቦ ይሰራል ብለዋል።

የመሠረተ ልማት ስራዎች መስፋፋት ህብረተሰቡ በአቅራቢያው የተሟላ የጤና አገልግሎት እንዲያገኝ ምቹ ሁኔታን መፍጠሩን የተናገሩት ደግሞ  የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር መልካሙ አብቴ ናቸው።

በዘርፉ በተሠራው ስራ  ውጤት መምጣቱን ጠቁመው፤ ጤና ሚኒስቴር ለክልሉ እያደረገ ላለው ድጋፍ አመሰግነዋል።

እንደ ክልል የጤና መሠረተ ልማቶችን በሰፊው ለማህበረሰቡ ተደራሽ ለማድረግ  በቀጣይ በዘርፉ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራ አስገንዝበዋል።

ለ3 ቀናት በሚቆየው የውይይት መድረክም የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱና የክልሎች የሥራ ክንውን ሪፖርት ቀርቦ የሚገምገም ሲሆን የቀጣይ የትኩረት አቅጣጫም ይቀመጣል ተብሎ ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም