በምዕራብ ወለጋ በበጀት ዓመቱ ከ112 ሺህ ለሚበልጡ ወጣቶች የስራ እድል ለመፍጠር ታቅዷል

128

ግምቢ፤ ነሐሴ 5/ 2014 (ኢዜአ) በምዕራብ ወለጋ ዞን በተያዘው የበጀት ዓመት ከ112 ሺህ ለሚበልጡ ወጣቶች የስራ እድል ለመፍጠር መታቀዱን የዞኑ የስራ ዕድል ፈጠራና ክህሎት ጽህፈት ቤት ገለጸ።

የጽህፈት ቤት  የ2014 በጀት ዓመት እቅድ አፈፃፀምና የተያዘው  በጀት ዓመት እቅድ ዙሪያ ዛሬ በግምቢ ከተማ  ከባለድርሻ አካላትጋር  ውይይት አካሄዷል።

የጽህፈት ቤቱ  ሃላፊ ወይዘሮ አልማዝ መኮንን በወቅቱ እንዳሉት፤ ባለፈው የበጀት ዓመት በአካባቢው  የፀጥታ ችግር የነበረ ቢሆንም 55 ሺህ ለሚጠጉ ወጣቶች የስራ ዕድል ተፈጥሯል።

በበጀት ዓመቱ የስራ እድል ለተፈጠረላቸው ወጣቶች ከ14 ሚሊየን ብር ብድርና 2ሺህ 981ሄክታር መሬት መሰጠቱን እንዲሁም የቆየ ብድር 44 ሚሊየን ብር ማስመለስ መቻሉን ተናግረዋል፡፡

በተያዘው የበጀት ዓመት ደግሞ  ከ112ሺህ ለሚበልጡ  ወጣቶች በ18ሺህ 875 ኢንተርፕራይዞች በመደራጀት በተለያዩ የስራ ዘርፎች ለማሰማራት መታቀዱን አስረድተዋል።

ማኑፋክቸሪንግ፣ግብርና፣ ከብት ማደልብና  ንግድ በዘመኑ ለወጣቶቹ የስራን እድል ለመፍጠር ትኩረት ከተደረገባቸው የስራ ዘርፎች መካከል እንደሚገኙበት ጠቅሰዋል።

ለዚህም 248 ሚለዮን ብር ብድር፣ 4ሺህ 630 ሄክታር መሬትና ግብአቶች ለወጣቶቹ እንደሚቀርብም አብራርተዋል፡፡

ወጣቱ የስራ እድል ተጠቃሚ እንዲሆን የባለ ድርሻ አካላት  ከጽህፈት ቤቱ ጋር በመሆን የበኩላቸውን  እንዲወጡ ወይዘሮ አልማዝ ጠይቀዋል፡፡

የምዕራብ ወለጋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሰሎሞን ታምሩ በበኩላቸው ፤ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ወጣቶች የስራ እድል ተጠቃሚ እንዲሆኑ የበኩላቸውን መወጣት እንደሚጠበቅባቸው አሳስበዋል፡፡

 መንግስት የወጣቶችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ  እየሰራ አንደሚገኝ ተናግረዋል።

በወይይት መድረኩ  የተሳተፉ ባለድርሻ አካላትም ለእቅዱ ስኬታማነት የድርሻቸውን ለመወጣት እንደሚጥሩ መግለጻቸውን የኢዜአ ሪፖርተር ከግምቢ ዘግቧል፡፡