የፌዴራል ፖሊስ እና የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር በትብብር ለመስራት የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረሙ

104

ነሐሴ 5 ቀን 2014 (ኢዜአ)ፌዴራል ፖሊስ እና የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር በትራንስፖርት ደህንነትና የህግ ማስከበር ስራ ትብብራቸውን ይበልጥ ለማጠናከር የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረሙ።

የመግባቢያ ስምምነቱን የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዳግማዊት ሞገስ እና የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል ተፈራርመዋል።

ሁለቱ ተቋማት በመንገድ ትራንስፖርት፣በአቬይሽን እና በባቡር ትራንስፖርት ደህንነት ጥበቃና ህግ የማስከበር ስራዎች ዙሪያ ትብብራቸውን ይበልጥ አጠናክረው ለመስራት የሚያግዝ መሆኑን ሚኒስትሯ ዳግማዊት ሞገስ ተናግረዋል።

በቅርብ የተጀመረው ብሔራዊ የታለመለትን የነዳጅ ድጎማ ህግና ሥርዓት ተከትሎ ተግባራዊ እንዲሆንም የሚያግዝ ነው ብለዋል።

የመግባቢያ ስምምነቱ በሂደት ውጤታማነቱ እየተገመገመ እንደሚቀጥልም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል፤ በትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ዘርፍ በትብብርና በጋራ እየሰራን እንገኛለን ብለዋል።

የዛሬው ስምምነትም በሁሉም የትራንስፖርት መስኮች የደህንነት ጥበቃና ህግ የማስከበር ስራዎችን ይበልጥ የሚያጠናክር መሆኑን ገልጸዋል።

ፌዴራል ፖሊስ በሁሉም መስክ በኢትዮጵያ የተጀመሩ ልማቶች እንዲሳኩ አስተማማኝ ሰላም ለመፍጠር ሌት ከቀን በመስራት ላይ መሆኑንም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም