ግድቡ የሃይል ፍላጎትን ከሟሟላት ባሻገር ለግብጽና ሱዳን በቂና የተመጣጠነ ውሃ የማግኘት ዋስትናቸውን የሚያረጋግጥ ነው- ምሁራን

350

ነሐሴ 5 ቀን 2014 (ኢዜአ) የታላቁ ህዳሴ ግድብ 2ኛ ተርባይን ኃይል ማመንጨት መጀመሩ የኢትዮጵያን የሃይል ፍላጎት ከሟሟላት ባሻገር ለግብጽና ሱዳን በቂና የተመጣጠነ ውሃ የማግኘት ዋስትናቸውን ለማረጋገጥ ወሳኝ ምዕራፍ መሆኑን የሀዋሳ ዩኒቨርስቲ ምሁሯን አስታወቁ።

የዩኒቨርስቲው ምሁራን የህዳሴ ግድብ 2ኛ ተርባይን ዛሬ ኃይል ማመንጨት መጀመቱን በማስመልክት ከኢዜአ ጋር ቆይታ አድርገዋል።

በሐዋሳ ዩኒቨርስቲ የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የውሃ ሀብት ምህንድስና ትምህርት ክፍል ተባባሪ ፕሮፌሰር ዶክተር ሞልቶት ዘውዴ ሀገሪቱ ትልቅ ወጀብ ውስጥ ሆና የግድቡ ግንባታ ሳይስተጓጎል በተያዘለት ሂደት መሄዱ ትልቅ ስኬት ነው ብለዋል።

2ኛው ዙር ተርባይን ሃይል ለማመንጨት መብቃቱን የሚያበስረው ዜና ዛሬ በመሰማቱ ዜጎች ቀሪዎቹም ተርባይነሮች ተጠናቀው ወደ ስራ ይገባሉ የሚል ተስፋ እንዲኖራቸው ያደርጋል ነው ያሉት።

የህዳሴው ግድብ የኃይል ፍላጎትን ከሟሟላት ባሻገር ለታችኞቹ ሀገራት በቂና የተመጣጠነ የውሃ ፍሰት የሚያስችል ግዙፍ ፕሮጀክት መሆኑን ጠቅሰዋል።

በተለይ ኃይል አመንጭቶ ከግድቡ የሚወጣው ውሃ ከደለል በጸዳ መልኩ የተጣራ በመሆኑ ከበታች የሚገኙ የሱዳንና የግብጽ ግድቦችን የአገልግሎት ዘመን የሚያራዝም ነው ብለዋል።

የግድቡን ዘላቂ አገልግሎት ለማረጋገጥ በግድቡ ተፋሰሶች የእጽዋት ልማት፣የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ ላይ መረባረብ እንደሚያስፈልግ ተባባሪ ፕሮፌሰር ሞልቶት አፅንዖት ሰጥተዋል።

በግድቡ ዙሪያ መንግስት እየተከተለ ያለው ጠንካራ የዲፕሎማሲ ስራም የሚደነቅ መሆኑን ተናግረዋል።

በዩኒቨርስቲው የውሃ ሀብትና መስኖ ምህንድስና ትምህርት ክፍል ረዳት ፕሮፌሰር ዶክተር ቴዎድሮስ አሰፋ በበኩላቸው እንደ ሀገር በ2014 ዓ/ም ኢትዮጵያ ያጋጠሟትን ችግሮችን ተቋቁማ 2ኛው ተርባይን ኃይል ማመንጨት እንዲጀመር መደረጉ እንዳስደሰታቸው ገልጸዋል።

ግድቦች ሲሰሩ ውሃ መያዛቸው ለኛ ኃይል በማመንጨት ከሚያስገኘው ጥቅም ባለፈ ለታችኞቹ ሀገራት ደለል ለማስቀረት እና 90 በመቶ የጎርፍ አደጋን እንደሚቀንስ ጥናቶች እንደሚያሳዩ አስረድተዋል።

ዛሬ ኃይል ማመንጨት የጀመረው ተርባይን ወደ ሀገሪቱ የኃይል ማሰራጫ ሲስተም ውስጥ ሲገባ አሁን ላይ የሚታየውን የሃይል መቆራረጥ ችግር በመቅረፍ ረገድ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው አውስተዋል።

በቀጣይም የግድቡ ግንባታ ሙሉ ለሙሉ ተጠናቆ ስራ ሲጀምር ንጹህ፣ዘላቂነት ያለውና በዝቅተኛ ዋጋ ለጎረቤት አገራት ጭምር የኤሌክትሪክ ኃይል በሽያጭ በማቅረብ ቀጠናዊ ትስስርን ለማጎልበት እንደሚያስችል ዶክተር ቴዎድሮስ አብራርተዋል።