በኢትዮጵያ ለተጀመረው አገራዊ ምክክር ስኬታማ ሂደት የሃይማኖት ተቋማት የድርሻቸውን እንዲወጡ ተጠየቀ

164

ነሀሴ 05/2014 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ ለተጀመረው አገራዊ ምክክር ስኬታማ ሂደት የሃይማኖት ተቋማት የድርሻቸውን እንዲወጡ የአገራዊ ምክክር ኮሚሽን ጥሪ አቀረበ።

የኢትዮጵያ ሙሉ ወንጌል አማኞች ቤተክርስቲያን የልማት ኮሚሽን እና የሰላም ሚኒስቴር በትብብር ያዘጋጁት በእምነት ተቋማት መካከል የሚደረግ የምክክር መድረክ ተካሂዷል።

በመድረኩ ከኢትዮጵያ አሁናዊ ተጨባጭ ሁኔታ አንፃር በሃይማኖቶች መካከል የሚደረግ ምክክር አስፈላጊነትና ለሰላም ያለው ፋይዳ ላይ ውይይት ተደርጓል።

የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ዶክተር ዮናስ አዳዬ፤ የሀይማኖት ተቋማት ለሀገር ሰላም ግንባታ እና አብሮነት መጠናከር የማይተካ ሚና ያላቸው መሆኑን ገልጸዋል።

ሀገራዊ ምክክሩ እውቀት መር ሁሉን አካታች መርህ  የሚከተል በመሆኑ የሃይማኖት ተቋማት ሚና ከፍተኛ ነው ብለዋል።

በመሆኑም ለሀገራዊ ምክክሩ ስኬት የሀይማኖት ተቋማት የበኩላቸውን ሚና ሊወጡ እንደሚገባ አፅኖት ሰተዋል።

ሰላምን ባህል ያደረገ ህዝብ እንዲዳብርና በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም እንዲመጣና ኮሚሽኑ የተጀመረውን ጥረት የሀይማኖት ተቋማት እንዲደግፉ  ጥሪ አቅርበዋል።

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ከመንበረ ፓትሪያሪክ ጠቅላይ ጽህፈት ቤት የገዳማት አስተዳዳር ሃላፊ  መላከ ህይወት ቆሞስ አባ ወልደጊዮርጊስ ታዬ፤ ሀገሪቷ ከድህነት አረንቋ እንድትወጣ የሀገር ሰላም  አስፈላጊ ነው ብለዋል።

በዚህ ረገድ ሀገራዊ ምክክሩ የጋራ መግባባት የሚያመጣና የሀገር ሰላም እንዲመጣም አስተዋፆ የሚያደርግ መሆኑን ተናግረዋል።

በመሆኑም የእምነት አባቶች ምዕመኖቻቸውን የሰላም አምባሳደር እንዲሆኑ ካስተማሩና ከመከሩ ሀገራዊ ምክክሩ ስኬታማ ይሆናል ሲሉ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ የእስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት የሰላምና የእርቅ ዘርፍ ሃላፊ ሃጂ ሙስጠፋ ናስር፤ ተመካክሮ መስራትና ማልማት የጋራ ስምምነት ስለሚኖረው ለሰላም አስተዋፆ አለው ብለዋል።

ሁሉም ቤተ-እምነቶች የተከታይ ምዕመኖቻቸው እረኞች በመሆናቸው ሰላምን በማምጣት ረገድ አስተዋፆ እንደላቸው ገልፀው በዚህ ረገድ ቤተ እምነቶች ሀላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ሙሉ ወንጌል አማኞች ቤተክርስቲያን የልማት ኮሚሽን ኮሚሽነር ዮሃንስ ሃይለማርያም በበኩላቸው ምክክሩ በሃይማኖት ተቋማት መካከል እርስ በእርስ መቀራረብና መደማመጥ እንዲኖር አጋዥ መሆኑን ገልጸዋል።

የአገራዊ ምክክሩ ዓላማ እንዲሳካ ሁሉም በኩሉን ድርሻ እንዲወጣ ጠይቀው መሰል መድረኮች ቀጣይነት እንድኖራቸው ጠይቀዋል።