በክልሉ የሚተከሉ ችግኞች የድርቅና የጎርፍ ተጋላጭነትን ለመቀነስ ሁነኛ መፍትሄ ናቸው -አፈ-ጉባኤ አስያ ከማል

132

ሰመራ፣ ነሐሴ 05 ቀን 2014(ኢዜአ) በአፋር ክልል የሚተከሉ ችግኞች ድርቅና የጎርፍ ተጋላጭነትን ለመቀነስ ሁነኛ መፍትሄ መሆናቸውን የክልሉ ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ወይዘሮ አስያ ከማል አስታወቁ።

የክልሉ የምክር ቤት አባላትና ሰራተኞች በአውሲ-ረሱ ዞን አፋምቦ ወረዳ ዛሬ የችግኝ ተከላ መርሃ-ግብር አካሂደዋል።

የክልሉ ምክር ቤት ዋና አፈ-ጉባኤ ወይዘሮ አስያ ከማል በወቅቱ እንዳሉት በክልሉ የሚተከሉ ችግኞች በክልሉ እየጨመረ የመጣውን የድርቅና የጎርፍ ተጋላጭነት ለመቀነስ ሁነኛ መፍትሄ ናቸው።

ዘንድሮ  እንደ ክልል የተያዘውን የአረንጎዴ አሻራ ልማት  መርሀ ግብር እቅድ ውጤታማ ለማድረግ አመራሩ ስራውን በባለቤትነት መምራት ይጠበቅበታል” ብለዋል።

“ህብረተሰብም የአየር ንብረት ለውጡ ዋንኛ ሰለባ በመሆኑ በየአካባቢው ችግኝ በመትከል  መንከባከብና ማልመት ባህሉ አድርጎ በመያዝ በረሃማነትን በመከላከል ለኑሮ ምቹ አካባቢን ለቀጣዩ ትውልድ ማስረከብ ይጠበቅበታል” ብለዋል።
በተለይም ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ያላቸውን አንደ  ማንጎ፣ ሙዝና ሎሚን ጨምሮ የተለያዩ ፍራፍሬዎችን ማልማት የአካባቢውን ገጽታ ከመቀየር በተጨማሪ ኑሮን ለማሻሻል  የሚያግዝና የገቢ አማራጭን የሚፈጥር በመሆኑ በችግኝ ተከላው በንቃት መሳተፍ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

የክልሉ ምክር ቤት አባላትና ሰራተኞች በዘንድሮ  የአረንጓዴ አሻራ ልማት እቅድ ስኬታማ እንዲሆን  ለማነቃቃት በወረዳው ተገኝተው 3 ሺ ችግኞች መትከላቸውን አመልክተዋል።

“የችግኝ ተከላ መርሃ-ግብሩ  ምቹ የኑሮ አካባቢ ከመፍጠር ባለፈ ለአርብቶ አደሩ  የእንስሳት መኖ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የሚያግዙ አማራጮችን በማስፋት ዘርፈ-ብዙ ጠቀሜታ አለው ” ያሉት ደግሞ የአፋምቦ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሁሴን አሊ ናቸው።

በወረዳው በተያዘው ክረምት 280ሺ ችግኞች የመትከል ስራ  መጀመሩን ጠቁመው እየተተከሉ ካሉት ችግኞች ውስጥ  ከ100ሺ በላይ የሚሆኑት ለምግብነት የሚውሉ መሆናቸውን ተናግረዋል ።

“ቀሪዎቹ ደግሞ  ለተለያዩ አገልግሎቶች የሚውሉ አገር በቀል ዝርያ ያላቸው መሆናቸውን አመልክተዋል።

የምክር ቤቱ አባላት በችግኝ ተከላ መርሃግብር መሳተፋቸው ለህብረተሰቡ መነቃቃት የሚፈጥር መሆኑን ገልጸዋል።

የክልሉ ምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴ አባል ወይዘሮ መዲና ኡመሮ በበኩላቸው “የችግኝ ተከላ መርሃ-ግብሩ እየተራቆቱ የመጡ ሀገር በቀል ዛፎች እንዲያገግሙ የሚረዳ መልካም ስራ ነው” ብለዋል።

በተለይም የዘንድሮ ክረምት ለችግኝ ተከላመርሃ-ግብሩ ምቹ በመሆኑ ሁሉም በየአካባቢው ችግኝ መትከልና መንከባከብ እንደሚገባው ተናግረዋል።

በአፋር ክልል በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ መርሃ ግብር  ከ14 ሚሊዮን በላይ የተለያዩ ችግኞች እንደሚተከሉ የክልሉ እንሰሳት፣ እርሻና ተፈጥሮ ሃብት ቢሮ  መረጃ አመላክቷል።