በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን ከቤት ንብረታቸው ለተፈናቀሉ ወገኖች 30 ሚሊዮን ብር የሚገመት ድጋፍ ተደረገ

120

ነቀምቴ ነሐሴ 05/2014 /ኢዜአ/ በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን ከቤት ንብረታቸው ለተፈናቀሉ ወገኖች 30 ሚሊዮን ብር የሚገመት ድጋፍ መደረጉን ዞኑ ቡሳ ጎኖፋ ጽህፈት ቤት አስታወቀ ፡፡

የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ ነገሮ ባኔ ለኢዜአ እንደገለጹት  የተደረገው ድጋፍ የወለጋ ዩኒቨርሲቲ፣ የመካነ ኢየሱስ ወንጌላዊት ቤተክርሲቲያን፣ ከክልሉ እና ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች የተገኘ ነው።

የምግብ እህል፣ አልባሳት፣ የቁሳቁስና  የአፈር ማዳበሪያ ድጋፉ የተደረገው አሸባሪው ሸኔ በፈጠረው የፀጥታ ችግር ምክንያት ከቤት ንብረታቸው ለተፈናቀሉ ከ9 ሺህ 170 ለሚበልጡ ወገኖች ነው ብለዋል።

እንደ ኃላፊው ገለጻ በዞኑ  አቤ ደንጎሮ፣ ጃርደጋ ጃርቴና የአሙሩ ወረዳዎች አንዳንድ አካባቢዎች ንጽሃን ዜጎች አሸባሪው ሸኔ በፈጠረው የፀጥታ ችግር መፈናቀላቸውን ተናግረዋል ።

አሸባሪው ሸኔ በዞኑ የተለያዩ አካባቢዎች  በፈጠረው የፀጥታ ችግር ምክንያት 54ሺህ ዜጎች የተፈናቀሉ ሲሆን፤ እስካሁን  15ሺህ ያህሉ ወደ ቄያቸው መመለሳቸውን ገልጸው፣ ለተፈናቃይ ወገኖች እየተደረገ ያለው ድጋፍ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል፡፡

ጃርደጋ ጃርቴ ወረዳ የሀርቡ ነጋሦ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር በየነ ሶሪ በሰጡት አስተያየት በአሸባሪው ሸኔ በደረሰባቸው ጥቃት ሁለት ልጆቻቸው እንደተገደሉባቸው፣  ሀብት ንብረታቸ ተዘርፉ ከቀያቸው መፈናቀላቸውን ተናግረዋል፡፡

በመንግስት በኩል የብርድ ልብስ፣ የምግብ እህል፣ የተለያዩ የቤት ቁሳቁሶችና የአፈር ማዳበሪያ ድጋፍ እንደተደረገላቸውና በዞኑ የቡሳ ጎኖፋ አማካይነት 3ሺህ ብር ጥሬ ገንዘብ እንደተሰጣቸው አስረድተዋል፡፡

የሆሮ ቡሉቅ ወረዳ የቦኔ አቡና ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ ምሥሬ ቀደመ በበኩላቸው በአካባቢያው የሽብር ቡድኑ በፈጠረው የፀጥታ ችግር ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው በሻምቡ ከተማ ኪራይ ቤት እንደሚኖሩ ገልጸዋል፡፡

የቀን ሥራ ሰርተው ቤተሰብን እንደሚያስተዳድሩ የሚናገሩት ወይዘሮ ምስሬ፣ የዞኑ የቡሳ ጎኖፋ ጽህፈት ቤት የ2 ሺህ 500 ብር  ድጋፍ እንዳደረገላቸው አስረድተዋል፡፡

ሸኔ መኖሪያ ቤታቸውን አቃጥሎ፣ ከብቶቻቸውን መዝረፉን ጠቅሰው ከቀያቸው ተፈናቅለው በአቅራቢያቸው በሚገኝ ጤና ኬላ ውስጥ ተጠልለው እንደሚገኙ የድድቤ ኪስታና ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር አብዲሳ ቆርቻ ገልጸዋል።

የዞኑ የቡሳ ጎኖፋ ጽህፈት ቤት 2 ሺህ 500 ብር  ድጋፍ አድርጎልኛል የሚሉት አርሶ አደር አብዲሳ ሸኔ በፈጠረው የፀጥታ ችግር የእርሻ ማሳቸው እንዳላረሱም ተናግረዋል፡፡