አንባቢ ትውልድ ለመፍጠር እየተሰራ ነው-አገልግሎቱ

165

ሀዋሳ ነሀሴ 5/2014 ኢዜአ በመላ ሀገሪቱ አንባቢ ትውልድ ለመፍጠር እየሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ ቤተ-መዛግብትና ቤተ- መጽሀፍት አገልግሎት አስታወቀ።

በኢትዮጵያ ቤተመዛግብትና ቤተ መጽሀፍት አገልግሎት የኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ገረመው ከበደ ለኢዜአ እንደገለጹት  በመላ ሀገሪቱ አንባቢ ትውልድ ለመፍጠር እየተሰራ ነው።

በዓመት ከ5 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት በመመደብ በሁሉም ክልሎች ለሚገኙ ቤተ-መጽሀፍትና የንባብ ማዕከላት ወቅታዊ የሆኑ መጽሀፍትን በመግዛት እየተሰራጨ መሆኑን ተናግረዋል።

በተያዘው ዓመት “በየክልሉ የንባብ ሳምንት በማዘጋጀት በየክልሎች በነፍስ ወከፍ ለአስር ትምህርት ቤቶች፣ የንባብ ማዕከላትና የህዝብ ትምህርት ቤቶች ከ5 ሺህ በላይ መጽሀፍትን ለግሰናል” ሲሉ አመልክተዋል።

ዳይሬክተሩ አክለው ደራሲያንና ማህበረሰብ አንቂዎችን በመጋበዝ ተሞክሯቸውን እንዲያካፍሉ የመቀስቀስና የማስተማር ስራ እየተሰራ መሆኑን  ጠቁመዋል።

የቤተ-መዛግብትና ቤተ-መጽሀፍት አገልግሎት የንባብ ልምድን ለማሳደግ በመላ ሀገሪቱ በመንቀሳቀስ የማነቃቃት ስራ እየሰራ እንደሚገኝ አስታውቀዋል ።

በጉዳዩ ላይ አስተያየታቸውን የሰጡ ጸሀፍትና አንባቢያን እንዳሉት የህብረተሰቡ  የንባብ ልምድ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተቀዛቀዘና እየቀነሰ መጥቷል።

ለንባብ ባህል መቀነስ የቴክኖሎጂና የመጽሀፍት ዋጋ መናር  አስትዋኦ እንዳለው ጠቅሰዋል።

የሀዋሳ ከተማ ነዋሪ የሆኑት አንባቢና ጸሀፊ ሻለቃ ጳውሎስ ጌታቸው "ዛሬ ላይ ከደረስንበት የቴክኖሎጂ እድገት አንጻር በወረቀት ከሚታተመው ይልቅ በቀላሉ የምንፈልገውን ብቻ በመምረጥ የምናነብበት አማራጭ በስልኮቻችን ማግኘታችን መጽሀፍ ገዝቶ የማንበብ ልምድ እንዲቀዛቀዝ ምክንያት ሆኗል" ብለዋል።

የተቀዛቀዘውን የንባብ ልምድ መልሶ ለማምጣት ቤተ-መጽሀፍትን በመገንባት እየተሰራ ያለው ስራ ተገቢ መሆኑን ጠቁመው  በሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎች በስፋት መከናወን እንደሚገባው ገልጸዋል።

አንባቢን ለመፍጠር ቤተሰብ ለልጆቹ መጽሀፍ በማንበብና ገዝቶ በመስጠት የሚጠበቅበትን ሀላፊነትና ግዴታ መወጣት እንዳለበት አመልክተዋል።

"በአሁኑ ወቅት የማህበራዊ ድረገጾች መበራከት አብዛኛው ማህበረሰብ ጊዜውን በነዚህ ድረገጾች ላይ እንዲያውል አድርጓል" ያለው ደግሞ በከተማው በንባብና በመጽሀፍት ዙሪያ የውይይት መድረክ በማዘጋጀት አንባቢ ለመፍጠር እየሰራ ያለው ጋዜጠኛ ደረጀ ሙሉጌታ ነው።

በከተሞች ከንባብ ማዕከላት ይልቅ ፑል ቤትና ሌሎች መዝናኛ ቤቶች በብዛት እየተከፈቱ ያሉበት ሁኔታ የአንባቢውን ጊዜ መያዛቸውን ጠቁሟል።

ጋዜጠኛ፣ ደራሲና የኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር የደቡብ ቅርንጫፍ ጸሀፊ ታሪኩ ሰብስቤ በበኩሉ “የመጽሀፍት ህትመት አሁንም አለ፤ እየታተመ ነው፤ ግን ዋጋቸው ከህዝቡ የመግዛት አቅም አንጻር ውድ መሆኑ የአንባቢ ቁጥር እንዲቀንስ ምክንያት ሆኗል” ብሏል።

"በየክልሎች የንባብ ማዕከላትንና ቤተ መጽሀፍትን በማስፋፋት አንባቢ ለማምጣት መንግስትም ህዝቡም በትኩረት ሊሰሩ ይገባል" ሲል  አመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም