ጉዳት ለደረሰባቸው የጤና ተቋማት 79 ነጥብ 3 ሚሊየን ብር ዋጋ ያላቸው የህክምና መሳሪያዎች ድጋፍ ተደረገ

115

ባህር ዳር ነሃሴ 5/2014 በአማራ ክልል አሸባሪው ህወሃት በከፈተው ጦርነት ጉዳት ለደረሰባቸው የጤና ተቋማት 79 ነጥብ 3 ሚሊየን ብር ዋጋ ያላቸው የህክምና መሳሪያዎችና ቁሳቁሶች ድጋፍ ተደረገ።

ፓዝ ፋይንደር ኢትዮጵያ ከአሜሪካ ዓለም አቀፍ የልማት ተራድኦ ድርጅት ባገኘው የገንዘብ ድጋፍ የገዛቸውን የህክምና መሳሪያዎችና ቁሳቁሶች ዛሬ  በባህር ዳር ከተማ ለክልሉ ጤና ቢሮ አስረክቧል።

በጤና ሚኒስቴር ከፍተኛ አማካሪና የጤና ተቋማት መልሶ ማቋቋም አስተባባሪ ዶክተር ማርታ ምንውዬለት በርክክብ ስነ ስርዓቱ ላይ እንዳሉት በአሸባሪው ህወሃት ወረራ የጤና ተቋማት ከፍተኛ ውድመትና ጉዳት ደርሶባቸዋል።

ሚንስቴሩ ከግብረ ሰናይ ድርጅቶች ጋር በመተባር የወደሙና ጉዳት የደረሰባቸውን የጤና ተቋማት ከበፊቱ የተሻለ አገልግሎት እንዲሰጡ ለማስቻል መልሶ የማቋቋም ስራ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

የጤና ተቋማቱን በማቋቋምና ለአገልግሎት በማብቃት ፓዝ ፋይንደር ኢትዮጵያ ቀደም ሲል ከ234 ሚሊየን ብር በላይ ግምት ያላቸው የህክምና መሳሪያዎችንና ቁሳቁሶችን ድጋፍ ማድረጉን አስታውሰዋል።

ድጋፉ የጤና ተቋማቱን በህክምና መሳሪያ፣ በመድሃኒትና ሌሎች ቁሳቁሶች እንዲሁም በሰው ሀይል መልሶ በማደራጀት በተለይም የእናቶችና ህጻናት ሞትን ለመቀነስ  የሚያስችል አቅም ለመፍጠር  አስተዋጾ ያለው መሆኑን ጠቁመው ድርጅቱ ዛሬም ላደረገው ድጋፍ  ምስጋና አቅርበዋል።

የፓዝ ፋይንደር ኢትዮጵያ ሃላፊ ዶክተር መንግስቱ አስናቀ በበኩላቸው ድርጅቱ ከአሜሪካ ዓለም አቀፍ የልማት ተራድኦ ድርጅት በሚያገኘው የገንዘብ ድጋፍ  የክልሉን ፍላጎት በመሰረት በማድረግ በጦርነቱ ጉዳት ለደረሰባቸው የጤና ተቋማት ድጋፍ ማድረጉን ተናግረዋል።

በዛሬው እለትም ከ79 ነጥብ 3 ሚሊየን ብር በላይ ዋጋ ያላቸው የቀዶ ጥገና ህክምና፣ የወሊድ፣ የሰመመን መስጫ፣ የደም መመርመሪያና ሌሎች ከፍተኛ የህክምና መሳሪያዎችና ቁሳቁሶችን  ድጋፍ ማድረጉን  አመልክተዋል።

ድጋፉ በተጨማሪም የላብራቶሪ፣ የስትራላይዜሽን፣ የልብስ ማጠቢያና ማድረቂያ ማሽን ጨምሮ ጤና ባለሙያዎችንና ታካሚዎችን ከብክለት የሚከላከሉ የህክምና ቁሳቁሶችን ያካተተ መሆኑን ጠቅሰዋል ።

"በድጋፍ የሚገኙ የህክምና መሳሪያዎችና ቁሳቁሶች ለታለመላቸው ዓላማ እንዲውሉ ትኩረት ሰጥተን እየሰራን ነው" ያሉት ደግሞ የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ሃላፊ ዶክተር መልካሙ አብቴ ናቸው።

አሸባሪው ህወሓት በክልሉ ላይ ጦርነት በመክፈት በጤና ተቋማት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማድረሱን አስታውሰው "በክልሉ   መረጋጋት ከሰፈነ ማግስት ጀምሮ መሰረታዊ የጤና አገልግሎቶችን ፈጥኖ ማስጀመር ተችሏል" ብለዋል።

የፌደራል መንግስት፣ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች፣ ዳያስፖራውና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች ያደረጉት ድጋፍ የሚበረታታ መሆኑን ተናግረዋል።

በጦርነቱ ወቅት በህክምና እጦት በእናቶችና ህጻናት የደረሰው ሞት፣ በንጹሃን ላይ በደረሰው የስነ ልቦና፣ የአካልና የአእምሮ ጉዳት ከፍተኛ በመሆኑ የሁሉንም አካላት ርብርብ የሚጠበቅ መሆኑን አስረድተዋል።

የወደሙ የጤና ተቋማትን በፊት አገልግሎት ይሰጡበት ከነበረው በተሻለ ለህብረተሰቡ እንዲያገለግሉ ለማስቻል እየተደረገ ባለው ጥረት ሁሉም በሚችለው የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም