የአፍሪካን ችግር በአፍሪካ መፍታት በሚለው መርህ የሰሜን ኢትዮጵያ የሰላም ሂደት እልባት እንዲያገኝ መንግሥት ጽኑ አቋም አለው- የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

197

ነሃሴ 5/2014/ኢዜአ/ የአፍሪካን ችግር በአፍሪካ መፍታት በሚለው መርህ የሰሜን ኢትዮጵያ የሰላም ሂደት እልባት እንዲያገኝ መንግሥት ጽኑ አቋም እንዳለው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ።

በሕገ-ወጥ መንገድ በኢትዮጵያ የሚኖሩ የውጭ ሀገራት ዜጎችን ህጋዊ የማድረግ ምዝገባም እስከ ነሐሴ 13 ቀን 2014 ዓ.ም ድረስ ተራዝሟል ተብሏል።

የሚኒስቴሩ ቃል-አቀባይ አምባሳደር መለስ አለም፤ በሰጡት መግለጫ በሕገ-ወጥ መንገድ በኢትዮጵያ የሚኖሩ የውጭ ሀገራት ዜጎችን ህጋዊ የማድረግ ምዝገባ እስከ ነሐሴ 13 ቀን 2014 ዓ.ም ድረስ ተራዝሟል።

የተራዘመበት ምክንያት ከአሁን በፊት በነበረዉ የምዝገባ ቀን ገደብ በተለያየ ምክንያት ያልተመዘገቡ የዉጭ ሀገራት ዜጎች በሕግ አግባብ እንዲንቀሳቀሱ ለመጨረሻ ጊዜ ዕድሉን ለመስጠት ነዉ።

ከሐምሌ 1 ቀን ጀምሮ በተጀመረው የውጭ ሀገራት ዜጎችን ወደ ሕጋዊ ሥርዓት የማስገባት ምዝገባ እስካሁን ከ36 አገራት የመጡ ከ70 ሺህ በላይ የውጭ ሀገራት ዜጎች መመዝገባቸውን ገልጸዋል።

ተመዝጋቢዎቹ ከካናዳ፣ አሜሪካ፣ ኮንጎ፣ ናይጄሪያ፣ የመን፣ ሶሪያ፣ ሱዳን፣ ደቡብ ሱዳን፣ ቻይና፣ ኤርትራ፣ቡሩንዲ፣ ጋና፣ ባንግላዲሽ፣ ሕንድ፣ ላይቤሪያ፣ ካሜሮንና የጣሊያን ዜጎች ይገኙበታል ብለዋል።

ምዝገባው በተለያዩ ቪዛ ገብተው ቪዛቸው እና የመኖሪያ ፈቃዳቸው የሚፀናበት ጊዜ ያለፈባቸው፤  ቪዛና የመኖሪያ ፈቃድ የሌላቸው፤ የስደተኝነት ዕውቅና የተፈቀደላቸው የውጭ ዜጎችን ይመለከታል።

ምዝገባው በአዲስ አበባ ከተማ፣ በኦሮሚያ ፊንፊኔ ዙሪያ ልዩ ዞን ከተሞችና ቢሾፍቱ ከተማ ወሳኝ ኩነት ምዝገባ ጽህፈት ቤቶች እንደሚካሄድ ገልጸዋል።

በሰሜኑ ኢትዮጵያ በተፈጠረው ግጭት ፖለቲካዊ መፍትሔ እንዲያገኝ በአፍሪካ ሕብረት አማካኝነት የተጀመረው የሰላም ጥረት እንዲቀጥል መንግሥት ጽኑ አቋም እንዳለው ተናግረዋል፡፡

በሌላ ምንም አይነት ተመሳሳይ ጥረት ተቀባይነት የለውም ያሉት ቃል-አቀባዩ፤ አስፈላጊ ከሆነ የአፍሪካ ሕብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልክተኛ የቀድሞ የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት ኦሊሴንጎ ኦባሳንጆን የሚደግፉ ከአፍሪካ ታዋቂ ሰዎች ቢጨመሩ ኢትዮጵያ አትቃወምም ብለዋል።

በትግራይ የመሰረታዊ አገልግሎት መጀመርን ለድርድሩ መንግሥት በቅድመ-ሁኔታነት አያስቀምጥም፤ ሆኖም አገልግሎቶቹን ለማስጀመር ምክክር እና ዝርዝር ውይይት ማድረግ ያስፈልጋል ነው ያሉት።

መንግሥት በማንኛውም ሰዓት በየትኛውም ቦታ ለሰላም ድርድር ዝግጁ መሆኑን ገልፀው፤ ይህም መንግሥት ወደ ሌላ ጦርነት የመግባት ፍላጎት የሌለው መሆኑንና ለሰላም ያለውን ቁርጠኝነት የሚያረጋግጥ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት ልክ እንደ ሕዳሴ ግድብ የአፍሪካ ችግር በአፍሪካ መፈታት አለበት የሚል ጽኑ አቋም ይዟል ነው ያሉት።

ሰሞኑን በማህበራዊ ሚዲያ እና በአንዳንድ ግለሰቦች እና ቡድኖች የአፍሪካ ሕብረት የፖለቲካ፣ ሰላም እና ፀጥታ ኮሚሽን አወጣዉ በሚል የሚያሰራጩት ሰነድ ህጋዊነት የሌለው የሐሰት ሰነድ መሆኑን ገልጸዋል፡፡