ኢክናስ የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ሁለተኛ ተርባይን ኃይል ማመንጨት አስመልክቶ ለኢትዮጵያውያን የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላለፈ

109

ነሐሴ 05 ቀን 2014(ኢዜአ) የኢትዮ-ካናዳውያን ኔት ወርክ ለማህበራዊ ድጋፍ (ኢክናስ) የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ሁለተኛ ተርባይን ኃይል ማመንጨት አስመልክቶ ለኢትዮጵያውያን የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላለፈ።

May be an image of 1 person and sitting

የተርባይኑ ኃይል ማመንጨት ማስጀመሪያ ስነ-ስርዓት ዛሬ ተካሄዷል።

በስነ-ስርዓቱ ላይ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድን ጨምሮ ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ፣ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን እንዲሁም ሌሎች ከፍተኛ የመንግሥት ሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።

የኢክናስ ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ ማርቆስ ተገኝ የሁለተኛው ተርባይን ኃይል ማመንጨት መጀመር ታሪካዊና ለኢትዮጵያ ትልቅ ትርጉም ያለው መሆኑን ለኢዜአ ገልጸዋል።

ምክትል ፕሬዝዳንቱ የግድቡ ኃይል ማመንጨት ልብን የሚያሞቅና የሚያስደስት ነው ብለዋል።

የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ኢትዮጵያውያን ልዩነቶች ቢኖሯቸውም በአገራቸው ጉዳይ እንደማይደራደሩ ያሳዩበት እንደሆነም ተናግረዋል።

በካናዳ የሚኖሩ የዳያስፖራ አባላት ለግድቡ ግንባታ የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉም ገልጸዋል።

ዛሬ ኃይል ማመንጨት የጀመረው 'ዩኒት' ዘጠኝ ሲሆን፥ 270 ሜጋ ዋት ኃይል የማመንጨት አቅም እንዳለው ተጠቁሟል።

የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ካሉት 13 የኃይል ማመንጫ ተርባይኖች መካከል የመጀመሪያው ተርባይን የካቲት 13 ቀን 2014 ዓ.ም ኃይል ማመንጨት መጀመሩ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም