በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከ2 ቢሊዮን ዶላር በላይ ዋጋ ያላቸው ምርቶችን በሀገር ውስጥ ምርት መተካት ተችሏል

99

ነሃሴ4/2014/ኢዜአ/   በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከ2 ቢሊዮን ዶላር በላይ ዋጋ ያላቸው ምርቶችን በሀገር ውስጥ ምርት መተካት መቻሉን የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ገለፀ።

ሚኒስቴሩ በሀገር አቀፍ ደረጃ ለመጀመሪያ ጊዜ በሚከናወነው የጸጥታ ተቋማት የአልባሳት አቅርቦት አፈፃፀም ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ተወያይቷል።

የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል በዚሁ ወቅት የጸጥታ አካላት አልባሳትን በሀገር ውስጥ ማምረት 'የኢትዮጵያ ታምርት' ንቅናቄ አካል መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

በዚህም የጸጥታ አካላትን አልባሳት በአገር ውስጥ በማምረት ከ60 በመቶ በላይ የውጭ ምንዛሬ ማዳን ተችሏል ነው ያሉት፡፡

በንቅናቄው የቴክኖሎጂ ሽግግር፣ የውጭ ምንዛሬ ማዳን እና ሰፊ የስራ እድል መፍጠር መቻሉን ገልፀው ይህንንም የበለጠ ውጤታማ ለማድረግ እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል።

አሁን ላይ ውስን ጥሬ እቃዎችን ከውጭ በማስገባት የጸጥታ አከላትን አልባሳት የማምረቱ ስራ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸው፤ በቀጣይ ሙሉ ለሙሉ ጥሬ እቃዎችን በአገር ውስጥ ለመተካት ይሰራል ነው ያሉት፡፡

የዓለም የገበያ ሁኔታ እጅግ ፈጣን በሆነ ሁኔታ እየተለዋወጠ መሆኑን ጠቅሰው፤ ከዚህ አኳያ በአገር ውስጥ ያለውን የምርት ፍላጎት በራስ አቅም ለመሸፈን እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በመሆኑም በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከ2 ቢሊዮን ዶላር በላይ ዋጋ ያላቸው ምርቶችን በሀገር ውስጥ ምርት መተካት መቻሉን አንስተው፤ ይህን የበለጠ ውጤታማ ለማድረግ በየዘርፉ የጋራ ጥረት ማድረግ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡

በጎረቤት አገራት ያለውን የገበያ እድል ለመጠቀም በትኩረት እየተሰራ ስለመሆኑም  አንስተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም