ዎዳ የብረታብረት ኩባንያ ወደ ኢንዱስትሪ ፓርክ ልማት ለማደግ የሚያስችለውን ስምምነት ከኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ጋር ተፈራረመ

192

ነሐሴ 4 ቀን 2014 (ኢዜአ) የቻይናው ዎዳ የብረታብረት ኩባንያ ወደ ኢንዱስትሪ ፓርክ ለማደግ የሚያስችለውን ስምምነት ከኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ጋር ተፈራረመ።

ኩባንያው እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጠር ከ2016 ጀምሮ የብረት ውጤቶችን በስፋት ሲያመርት የቆየ ሲሆን በዚህም ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በመቀነስ ረገድ ሚናውን እየተወጣ እንደሚገኝ ነው የተገለጸው።

አሁን ላይ ደግሞ ኩባንያው ወደ ኢንዱስትሪ ፓርክነት ለማደግ ከኢንቨስትመንት ኮሚሽን ጋር የመግባቢያ ስምምነትም ተፈራርሟል።

በስምምነቱ መሰረት ኩባንያው “አልፋ እና ዲዩንሴራሚክስ” ከተሰኙ ድርጅቶች ጋር በመሆን በኦሮሚያ ክልል ሰበታ ከተማ የኢንዱስትሪ ፓርክ የሚያቋቁሙ ይሆናል።

የኢንቨስትመንት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ዳንኤል ተሬሳ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት፤ኮሚሽኑ የአገር ውስጥና የውጭ ባለሃብቶች ኢንቨስትመንታቸውን እንዲያስፋፉ ድጋፍ እያደረገ ይገኛል።

ከዎዳ ብረታ ብረት ኩባንያ ጋር የተደረገው ስምምነት የድጋፉ አካል መሆኑን ጠቁመው ኩባንያው ወደ ኢንዱስትሪ ፓርክ የሚያድገው በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ቦርድ ውሳኔ መሆኑም አክለዋል።

ዎዳ ኩባንያ በኢንዱስትሪ ፓርክ ልማት ላይ ለመሳተፍ እንቅስቃሴ መጀመሩ የሚበረታታ እና ለሌሎች ባለሃብቶች አርዐያ እንደሚሆን ጠቅሰዋል።

እንደ ምክትል ኮሚሽነሩ ገለጻ በኩባንያው የሚለማው የኢንዱስትሪ ፓርክ በስራ እድል ፈጠራ፣የውጭ ምርቶችን በመተካትና በእውቀት ሽግግር ላይ የሚኖረው ፋይዳ ትልቅ ነው።

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን የግል አልሚዎች ወደ ኢንዱስትሪ ልማት እንዲገቡ የተለያዩ ማበረታቻዎችና አሰራሮችን መዘርጋቱን ጠቅሰዋል።

የዎዳ ብረታ ብረት ኩባንያ ኃላፊ ስቴቨን ሱኢ በበኩላቸው የኢንዱስትሪ ፓርኩ 95 ሚሊዮን ዶላር በሚጠጋ ወጪ እንደሚቋቋም ገልጸዋል።

ኢንዱስትሪ ፓርኩ በመነሻ ደረጃ ሲቋቋም ከ3 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች ቋሚና ጊዜያዊ የስራ እድል ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ኃላፊው ተናግረዋል፡፡

ፓርኩ በአጠቃላይ 100 ሄክታር መሬት ላይ የሚያርፍ መሆኑን የተናገሩት ኃላፊው እስካሁን የፓርኩ 20 ሄክታር መልማቱን አስረድተዋል።

ቀሪ ስራዎችን በፍጥነት በማጠናቀቅ ፓርኩ በሚቀጥሉት ሦስት ዓመታት ውስጥ ስራ እንዲጀምር ርብርብ እንደሚደረግም አክለዋል።

ፓርኩ ሥራ ሲጀምር መኪና መገጣጠሚያዎች፣የቤት ውስጥ ኤሌክትሮኒክስ ቁሳቁሶችን ጨምሮ በርካታ ምርቶች እንዲመረቱ የሚያስችል መሆኑንም ተጠቅሷል።

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ