ለሰባተኛ ጊዜ በሚካሄደው የቱርክ አፍሪካ ንግድ ፎረም ኢትዮጵያ በልዩ የክብር እንግድነት ትሳተፋለች

118

ነሐሴ 4 ቀን 2014 (ኢዜአ) ለሰባተኛ ጊዜ በሚካሄደው የቱርክ አፍሪካ ንግድ ፎረም ኢትዮጵያ በልዩ የክብር እንግድነት እንደምትሳተፍ የቱርክ ዓለም አቀፍ የኢንዱስትሪ ትብብር ፎረም አስታውቋል።

የቱርክ ዓለም አቀፍ የኢንዱስትሪ ትብብር ፎረም ፕሬዝዳንት ኡታኩ ብኒጊሱ ለሰባተኛ ጊዜ በቱርክ አንካራ የሚካሄደውን የቱርክ አፍሪካ ንግድ ፎረም አስመልክቶ በሰጡት መግለጫ ፎረሙ በቱርክ ዋና ከተማ አንካራ መስከረም 14 እና 15 ቀን 2022 እንደሚካሄድ ተናግረዋል።

በፎረሙ ከ1 ሺህ 250 በላይ በንግድ እና ቢዝነስ የተሰማሩ አፍሪካዊያን እንደሚሳተፉ ገልፀው፤ ኢትዮጵያም በዘንድሮው ዓመት በሚካሄደው ፎረም በልዩ የክብር እንግድነት እንደምትሳተፍ ጠቅሰዋል፡፡

በዚህም በፎረሙ ለሚሳተፉ አንድ መቶ ለሚሆኑ ኢትዮጵያዊያን የንግድና ቢዝነስ ሰዎች ልዩ የአገልግሎት ቅናሽ ይደረግላቸዋል ነው ያሉት፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የቱርክና አፍሪካ ግንኙነት እየተጠናከረ መምጣቱን ጠቅሰው፤ ዓለምአቀፍ ትብብር ፎረሙም ይህን ወዳጅነት የበለጠ በማጠናከር ረገድ የበኩሉን አስተዋጽኦ እየተወጣ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ