በሲዳማ ክልል የፖለቲካ ፓርቲዎች በጋራ በሚያሰሩ ጉዳዮች ላይ በመተባበር ውጤታማ መሆናቸው ተገለጸ

98

ሐዋሳ፣ ነሐሴ 04 ቀን 2014 (ኢዜአ) በሲዳማ ክልል የፖለቲካ ፓርቲዎች ዴሞክራሲ እንዲጎለብትና መልካም አስተዳደር እንዲረጋገጥ በጋራ በሚያሰሩ ጉዳዮች ላይ በመተባበር ውጤታማ መሆናቸውን የሲዳማ ክልል የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ገለጸ።

ሶስት ክልላዊ እና ዘጠኝ ሀገራዊ የፖለቲካ ፓርቲዎችን በአባልነት ያቀፈው የሲዳማ ክልል የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ጉባዔ ዛሬ በሀዋሳ ከተማ ተካሂዷል።

የብልጽግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራር እና የሲዳማ ክልል የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ አቶ የኋላሸት በቀለ እንዳሉት፤ የጋራ ምክር ቤቱ አባል የሆኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች በጋራ በሚያሰሩ ጉዳዮች ላይ በትብብር ይሰራሉ።

የጋራ ምክር ቤቱን ሲመሩ የነበሩት አምስቱ ስራ አስፈጻሚዎች በዛሬው ጉባዔ በአዲስ ስራ አስፈጻሚዎች መተካታቸውን የገለጹት ሰብሳቢው፤ ምክር ቤቱ ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ፓርቲዎች በሀሳብ የበላይነት የሚያምን አባላትን እንዲያፈሩ የቀጣይ የትኩረት አቅጣጫ መቀመጡን ተናግረዋል።

በክልሉ ዘላቂ ሰላምን ማረጋገጥ፣ የተጀመሩ የልማት እና የመልካም አስተዳደር ጉዳዮች ማስቀጠል ምክር ቤቱ አበክሮ የሚሰራቸው ጉዳዮች እንደሚሆኑም ጠቁመዋል።

የብልፅግና ፓርቲ የሲዳማ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አብርሃም ማርሻሎ በበኩላቸው የጋራ ምክር ቤቱ አባላት በልማት፣ በመልካም አስተዳደር፣ በዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታና ሀገራዊ ችግርን በመፍታት ረገድ በትብበርና በመተጋገዝ መንፈስ እየሰሩ እንደሚገኙ ገልጸዋል።

አባላቱ ከመንግስትና ከህዝብ ጎን በመሰለፍ ገንቢ ሚና መጫወታቸውን ጠቅሰው፤ ለመድብለ ፓርቲ ሥርዓት መጎልበት ብርቱ ሚና መጫወታቸውን ተናግረዋል።

ለክልሉ ሰላም መሆን አስተዋጽኦ ከማበርከት ባለፈ በህልውና ዘመቻ ወቅት ግንባር ድርስ በማቅናት ለሀገር መከላከያ ሰራዊት የተለያየ ድጋፍ ማድረጋቸውን አስታውሰዋል።

ተፎካካሪ ፓርቲዎች በክልሉ መንግስት ካቢኔ ውስጥ ተካተው በየደረጃው በሚገኙ መዋቅሮች እንዲሳተፉ መደረጉን አቶ አብርሃም ገልጸዋል።

የክልሉ መንግስትና ምክር ቤት የፖለቲካ ፓርቲዎችን መተባበር እና መተጋገዝ ለማቀላጠፍ የጋራ ምክር ቤቱን በፋይናንስና በሎጂስቲክስ በመደገፍ በቅርበት እንደሚሰራ ተናግረዋል።

የጋራ ምክር ቤቱ ፀሐፊና የህብር ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ አባልና የአደረጃጀት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ታምራት አሰፋ የጋራ ምክር ቤት አባላት በክልሉ ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች  ላይ ገንቢ አስተዋጽኦ እያደረጉ መሆኑን ጠቁመዋል።

አባላቱ ክፍተቶች ላይ አስተያየት ከመስጠት ባለፈ የመፍትሄ አካል በመሆን አስተዋጽኦ እያበረከቱ እንደሚገኙ አመልክተዋል።

በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የህዝቡ የልማት እና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ፈጣኝ ምላሽ እንዲያገኙ፣ በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር፣ በክልላዊና በሀገራዊ አንገብጋቢ ጉዳዮች ላይ  የምክር ቤቱ አባላቱ የነቃ ተሳትፎ  ማድረጋቸውን አውስተዋል።

የኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራሲ ፓርቲና የምክር ቤቱ አባል በለጠ ሰጌቦ በክልሉ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ለሰላም ቅድሚያ ሰጥተው ሲንቀሳቀሱ እንደነበር አስታውሰዋል።

በቀጣይም ሀገርን በማስቀደም በህግ ማዕቀፍ ውስጥ በመንቀሳቀስ ለሀገር የሚጠቅም ተሳትፎ እንደሚያደርጉ አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም