በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል የሚገኙ ሶስት ተቋማት የፋይናንስ መመሪያ በመጣስ ከ59 ሚሊዮን ብር በላይ ግዢ ፈጽመዋል- የክልሉ ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት

139

ቦንጋ፣ ነሐሴ 4 ቀን 2014 (ኢዜአ) በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል የሚገኙ ሶስት ተቋማት የፋይናንስ መመሪያ በመጣስ ከ59 ሚሊዮን ብር በላይ ግዢ መፈጸማቸውን የክልሉ ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት አስታወቀ።

የክልሉ ምክር ቤት መደበኛ ጉባኤ ዛሬ በሁለተኛ ቀን ውሎው የተለያዩ አጀንዳዎችን ተመልክቷል።

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት የ2014 ዓ.ም በጀት የኦዲት ሪፖርት ለምክር ቤቱ አቅርቧል።

የክልሉ ኦዲተር መስሪያ ቤት ኃላፊ አቶ አስራት አበበ በተወሰኑ ተቋማት የተዘጉ መዝገቦች ላይ ባደረገው የኦዲት ስራ ከአሰራር ውጭ በሆነ መንገድ የተከፈለና የተመዘገበ ገንዘብ መገኘቱን ገልጸዋል።

የሚዛን አማን ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ፣የቤንች ሸኮ ዞን የፋይናንስና የኢኮኖሚ ልማት መምሪያ እና የሰሜን ቤንች ወረዳ የፋይናንስና የኢኮኖሚ ልማት ጽህፈት ቤት ከፋይናንስ መመሪያ ውጪ 59 ሚሊዮን 572 ሺህ ብር ግዢ መፈጸማቸውን አመልክተዋል።

እንደዚሁም በመስተንግዶ ወጪ ከ3 ሚሊዮን ብር በላይ የመስተንግዶ ወጪ መመሪያን በመጣስ ወጪ ማድረጋቸውን ተናግረዋል።

በኦዲት ስራው የጥሬ ገንዘብ ቆጠራና ሪፖርት፣በቼክ የሚደረግ ክፍያ፣ የገቢ ሂሳብ፣ በሂሳብ እንቅስቃሴ መዝገብ ያልተመዘገቡ የወጪ ሂሳቦች፣ ለረጅም ጊዜ እየተንከባለሉ የመጡ ሂሳቦች እና መመሪያን ያልተከተለ የውሎ አበል ክፍያዎች እንደሚፈጸሙ ግኝቶች ያሳያሉ ብለዋል ዋና ኦዲተሩ።

ለመስተንግዶና ለድጋፍ የሚሰጡ የድጎማ የወጪ ሂሳቦች ለሃብት ብክነት በር ከፋች እየሆኑ እንዳለ የሚያመላክቱ ሁኔታዎች እየታዩ መሆኑንም አመልክተዋል።

ግኝቶች እንዲመለሱ የክልሉ ምክር ቤት አፈጻጸሙን መከታተል አለበት ያሉት አቶ አስራት ሕዝቡ ብልሹ አሰራሮችን መከላከልና የተጠያቂነት ስርዓት እንዲሰፍን አስተዋጽኦ እንዲያደርግ ጠይቀዋል።

የምክር ቤቱ አባላት የሕዝብና የመንግስት ውስን ሀብት ለታለመለት አላማ እንዲውል ብልሹ አሰራርን መዋጋት ይገባል ብለዋል።

የሚታዩ ብልሹ አሰራሮችን ለማስቀረት የክትትል እና የቁጥጥር ስርአቱን ተጠያቂነት እንዲኖረው በማድረግ በየደረጃው የሚታዩ የአሠራር ግድፈቶችን የማረም ስራ እንደሚከናወን ገልጸዋል።

በተያያዘ ዜና የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ምክር ቤት ለ2015 ዓ.ም በጀት ዓመት 11 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር በላይ በጀት በሙሉ ድምጽ አጽድቆታል።

በጀቱ ከክልሉ መንግስት ከሚሰበሰበው የውስጥ ገቢ፣ ከፌደራል መንግስት ድጎማ እና ከሌሎች የገቢ ምንጮች ከሚገኝ ገንዘብ እንደሆነ ተገልጿል።

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ