በዳኝነት ስርዓቱ ውስጥ ሙስና እና ብልሹ አሰራሮችን በዘላቂነት ለመከላከል የሚያግዝ ስትራቴጂ ተዘጋጅቷል

141

ነሐሴ 04 ቀን 2014 (ኢዜአ) በዳኝነት ስርዓቱ ውስጥ ሙስና እና ብልሹ አሰራሮችን በዘላቂነት ለመከላከል የሚያግዝ ስትራቴጂ ማዘጋጀቱን የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት አስታወቀ።

የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት መዓዛ አሸናፊ በፌደራል ፍርድ ቤቶች የ2014 በጀት ዓመት አፈጻጸምና የ2015 ዋና ዋና የትኩረት አቅጣጫዎች ላይ ዛሬ መግለጫ ሰጥተዋል።

በበጀት አመቱ በዳኝነት ነጻነት፣ በአገልግሎት ቅልጥፍና፣ በአገልግሎት ጥራት፣ በዳኝነት ተጠያቂነትና ተደራሽነትን ዙሪያ የተከናወኑ ዋና ዋና ተግባራትን አብራርተዋል።

የዳኝነት ነጻነትን ከማረጋገጥ በተጓዳኝ ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ የተከናወኑ ስራዎችን ዘርዝረዋል።

በዳኝነት አገልግሎት ላይ የሚስተዋሉ የስነ-ምግባር ግድፈቶች፣ የዲስፕሊን ጥሰቶችና የወንጀል ተግባራት የሚፈጽሙ ዳኞችም ሆኑ የአስተዳደር ሰራተኞች ተጠያቂ የሚያደርግ ስርአት መዘርጋቱን በመግለጫቸው አንስተዋል።

May be an image of 6 people, people sitting, people standing and indoor

በዚህም በዳኝነት ስርዓቱ ውስጥ ሙስናና ብልሹ አሰራሮችን በዘላቂነት መከላከል የሚያግዝ ስትራቴጂ መዘጋጀቱን ጠቅሰዋል።

ከፍርድ ቤቶች ጋር በተያያዘ ከሚነሱ የመልካም አስተዳደር ችግሮች ሙስና ዋነኛው መሆኑን ጠቅሰው፤ በማስረጃ ላይ የተመሰረቱ የሙስና ድርጊቶች ሲያጋጥሙ የዳኞች አስተዳደር ጉባኤ ፈጣን እርምጃ እንደሚወስድ ጠቁመዋል።

ለአብነትም የፍትህ ሚኒስቴር የተደራጀ የምርመራ ሪፖርት ባቀረበባቸው ሁለት ዳኞች ላይ የመከሰስ መብታቸው እንዲነሳ በማድረግ ከስራ ታግደው ጉዳያቸው በፍርድ ቤት እየታየ መሆኑን ገልጸዋል።

በተመሳሳይ የዳኞች አስተዳደር ጉባኤ ማስረጃ የቀረበባቸው ሌሎች ሁለት ዳኞችን ጉዳይ እንደሚመለከት አክለዋል፡፡

በዳኝነት ስርዓቱ ውስጥ የሙስና ወንጀልን ለመከላከል የተዘጋጀው ስትራቴጂ ላይ የጥቆማ ስርዓት መዘርጋቱን ጠቅሰው፤ በዚህም ተጨባጭ መረጃ ያለውን የትኛውንም አካል ጥቆማ ለመቀበል ዝግጁ መሆናቸውንም ነው ያብራሩት፡፡

ዳኞች ህግና ህሊናቸውን ብቻ ተከትለው በነጻነት ውሳኔ እንዲሰጡ አስፈላጊ ሁኔታዎች መመቻቸታቸውን የገለጹት ፕሬዝዳንቷ የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ የሚሰራው ስራ በቀጣይም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

በ2014 በጀት አመት በፌደራል ፍርድ ቤቶች 176 ሺህ 797 መዛግብት እልባት ማግኘታቸውን በመግለጫቸው አንስተዋል።

የሰው ሃይል ማነስ፣ የእውቀት ውስንነት፣ አመቺ የስራ ቦታ አለመኖር፣ የግብአት እጥረት በበጀት አመቱ ካጋጠሙ ችግሮች ውስጥ ጠቅሰዋል።

የተጠያቂነት ስርአት ማስፈጸሚያ ስልቶችንና አደረጃጀቶችን በማጠናከር፣ ከሙስና የጸዳ፣ ጥራት ያለው ፍትሃዊ ዳኝነት የሚሰጥበት ፍርድ ቤቶችን እውን ለማድረግ አስፈላጊውን እርምጃ መውሰድ የ2015 በጀት አመት ትኩረቶች ውስጥ ተጠቅሷል።

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም