የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ከስምንት ዩኒቨርሲቲዎች ጋር የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረመ

216

ነሐሴ 04 ቀን 2014 (ኢዜአ) የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር (ኢመደአ) እና በጥናት እና ምርምር መስከ የተሰማሩ ስምንት ዩኒቨርሲቲዎች በሳይበር ደህንነት ዘርፍ በጥናትና ምርምር፣ አቅም ግንባታ እና በታለንት ልማት ዙሪያ በጋራ ለመስራት የሚያስችላቸውን የጋራ ስምምነት ተፈራረሙ፡፡

ተቋሙ ከጎንደር ዩኒቨርሲቲ፣ ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ፣ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ፣ ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ፣ ሐረማያ ዩኒቨርሲቲ፣ አዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ፣ አዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ እንዲሁም ከኢትዮጵያ መከላከያ ዩኒቨርሲቲ ጋር ስምምነቱን ተፈራርሟል።

በፊርማ ስነስርዓቱ ላይ የተገኙት የኢመደአ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን ሶካ እንዳሉት፤ የትብብር ሰነዱ በሳይበር ደህንነት ዙሪያ ብቁ የሆነ የሰው ኃይልን ለማፍራት፣ በዩኒቨርሲቲዎች የሚሰሩት ጥናትና የምርምር ውጤቶች በተጨባጭ ወደ ተግባር የሚውሉበት አስቻይ መደላድል ለማመቻቸት እና በሳይበር ደህንነት ዙሪያ ልዩ ተሰጥኦ (Talent) ያላቸውን ታዳጊ ወጣቶችን ለመደገፍ እና ለማፍራት ያለመ ነው።

የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተወካዮች በበኩላቸው በኢንፎርሜሽን እና ቴክኖሎጂ ዙሪያ በየተቋሞቻቸው የትምህርት መርሃ ግብሮችና ማዕከላት እንዳሉ አንስተው፤ የሳይበር ደህንነት የጥናትና ምርምር እንዲሁም የሳይበር ታለንት ማልማት ላይ በትብብር ለመስራት ስምምነት ማድረጋቸው ትልቅ አቅም እንደሚሆናቸው ገልፀዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም