የጅማ ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታል እና ሀረር ሆስፒታል የካንሰር ጨረር ህክምና መስጠት ጀመሩ

አዲስ አበባ ነሃሴ 04 ቀን 2014(ኢዜአ) የጅማ ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታል እና ሀረር ሆስፒታል የካንሰር ጨረር ህክምና መስጠት መጀመራቸውን የኢትዮጵያ መድሃኒት አቅራቢ አገልግሎት ገለጸ።

ለሁለቱ ሆስፒታሎች የካንሰር ጨረር ህክምና መስጫ ማሽን ተገዝቶ የተገጠመላቸው ሲሆን ለሀዋሳ፡ ጎንደር እና ቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታሎችም የማሽን ተከላ ስራ እየተከናወነ መሆኑ ታውቋል።

የኢትዮጵያ መድሃኒት አቅራቢ አገልግሎት ምክትል ዳይሬክተር ሰለሞን ንጉሴ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ካንሰርን ጨምሮ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን ለመከላከል የተለያዩ የህክምና መሳሪያዎች ግዢ እየተፈጸመ ይገኛል፡፡

በ2014 ዓ.ም ለካንሰር ጨረር ህክምና መስጫ ማሽኖችና የህክምና መገልገያ መሳሪያዎች ግዢ ከ3 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ መደረጉን ተናግረዋል፡፡

ከጨረር ህክምና መስጫ ማሽኖች በተጨማሪ 'ሲቲስካን' እና 'ኤም.አር.አይ' የሚባሉ የዘመናዊ ማሽኖች ግዥ መከናወኑን ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ብቻ ይሰጥ የነበረው የካንሰር ጨረር ህክምና ከአገልግሎት ፈላጊው አንፃር በቂ አልነበረም ብለዋል።

አሁን ላይ ግን በስድስት ሆስፒታሎች ህክምናውን የመስጠት እቅድ ተይዞ እየተሰራ ሲሆን የጅማ ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታል እና ሀረር ሆስፒታል የካንሰር ጨረር ህክምና መስጠት መጀመራቸውን ተናግረዋል።

በቀጣይም  በሀዋሳ፡ በጎንደር እና በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታሎች የማሽን ግዢ ተፈፅሞ የተከላ ስራ እየተከናወነ መሆኑን ጠቁመዋል።

በአጠቃላይ አገልግሎቱ ለካንሰር ጨረር ሕክምና ማሽን ግዢ 1 ነጥብ 1 ቢሊዬን ብር ወጪ ማድረጉንም ምክትል ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።

ከዚህ በተጨማሪም ከፍተኛ እጥረት የሚታይባቸው የ'ኤም.አር.አይ' እና የ'ሲቲስካን' ማሽኖች ግዢ መፈፀሙን ተናግረዋል።

በዚህም የ14 የ'ሲቲስካን' ማሽንና ሰባት 'ኤም.አር.አይ' ግዢ ሂደት መጠናቀቁን ጠቅሰው በጴጥሮስ፣ አዳማ፣ ጳውሎስ፣ ዋቻሞ እና ወራቤ ሆስፒታሎች ስራ ይጀምራሉ ብለዋል።

ለ'ሲቲስካን'ና ለ'ኤም.አር.አይ' ማሽኖች ተከላ ከ2 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ ማድረጉንም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም