ድርጅቱ ለወደሙ ጤና ተቋማትና ተፈናቃዮች 10 ሚሊዮን ብር ግምት ያላቸው ቁሳቁሶችና የምግብ ድጋፍ አደረገ

113

ደሴ ነሀሴ 4/2014 (ኢዜአ) ቤዛ ፖስቲሊቲ የተባለ የልማት ድርጅት አሸባሪው ህውሃት በከፈተው ጦርነት ለወደሙ ጤና ተቋማትና ተፈናቃዮች 10 ሚሊዮን ብር ግምት ያላቸው ቁሳቁሶችና የምግብ ድጋፍ አደረገ።

የቤዛ ፖስቲሊቲ የልማት ድርጅት ሃላፊ አቶ ሰይድ አህመድ እንደገለፁት ድርጅቱ ድጋፉን ያደረገው  ከአሜሪካ ዓለም አቀፍ የልማት ተራድኦ ድርጅት /USAID/  በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ ነው።

ድጋፉ በጦርነቱ ለወደሙ 10 የጤና ተቋማትና ከተለያዩ አካባቢዎች ተፈናቅለው በኮምቦልቻ ከተማ ለተጠለሉ ተፈናቃዮች የሚውል መሆኑን ተናግረዋል።

ድጋፉ የተለያዩ የህክምና መገልገያ ቁሳቁሶችን ጨምሮ የሩዝ፣ የዳቦ ዱቄት፣ የዘይትና ሌሎች የንጽሕና መጠበቂያዎችን ያካተተ መሆኑን አመልክተዋል።

ድርጅቱ ተቋማትንና ተፈናቃዮችን መልሶ ለማቋቋም እየተከናወነ ባለው ስራ የድርሻውን ለመወጣት ድጋፉን ማድረጉን ጠቁመው ተጨማሪ ድጋፍ ለማድረግ ከባለድርሻ አካላት ጋር እየተሰራ መሆኑን  ገልጸዋል ።

የኮምቦልቻ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ መሃመድ አሚን የሱፍ ድጋፉን ሲረከቡ እንደገለጹት መንግስት ተፈናቃዮችን ለመደገፍና የወደሙ ተቋማትን መልሶ ለማቋቋም  ከአጋር አካላት ጋር በቅንጅት እየሰራ ነው።

በከተማው ከ6 ሺህ በላይ ተፈናቃዮች መኖራቸውን ጠቁመው “ዛሬ የተደረገው ድጋፍ ችግሩን ለማቃለል ስለሚያግዝ እናመሰግናለን” ብለዋል።

“በጦርነቱ የወደሙ ተቋማትን በቅንጅት መልሶ ማቋቋምና ተፈናቃዮችን መደገፍ የሁሉም ድርሻ ነው” ያሉት ደግሞ በአማራ ክልል አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ማስተባበሪያ ኮሚሽን የቅደመ ማስጠንቀቂያ ባለሙያ አቶ ጌቴ ምህረቴ ናቸው።

በክልሉ ከ824 ሺህ በላይ ተፈናቃዮች መኖራቸውን ጠቁመው ዛሬ ለተደረገው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።