በመጠለያ ጣቢያዎች ተላላፊ በሽታዎችን አስቀድሞ የመከላከል ተግባራት እየተከናወኑ ነው-መምሪያው

98

ሰቆጣ ነሃሴ 4/2014 (ኢዜአ) በዋግ ኽምራ ብሄረሰብ አስተዳደር ዞን ተፈናቃዮች በሚገኙባቸው መጠለያ ጣቢያዎች ተላላፊ በሽታዎችን አስቀድሞ የመከላከል ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን የዞኑ ጤና መምሪያ አስታወቀ።

የመምሪያው ምክትል ሃላፊ አቶ አሰፋ ነጋሽ ለኢዜአ እንደገለፁት በዞኑ ተፈናቃዮች በሚገኙባቸው መጠለያ ጣቢያዎች ተላላፊ በሽታዎችን አስቀድሞ ለመከላከል የሚያስችሉ የተለያዩ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች እየተከናወኑ ነው።

በመጠለያ ጣቢያዎቹ  በርካታ ተፈናቃዮች ባንድ ላይ በተጨናነቀ ሁኔታ በመኖራቸው ሊከሰቱ የሚችሉ እንደ አተት፣ ታይፈስ፣ ታይፎይድ፣ ወባና ሌሎች ተላላፊ በሽታዎችን አስቀድሞ ለመከላከል እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል ።

ችግሩን ለመቅረፍ የዞኑ መስተዳድር ከዘርፉ አመራሮች ጋር በመሆን በሽታዎችን ለመከላከል የሚያስችል የቅድመ ማስጠንቀቂያ ምላሽ ሰጭ ግብረ ሃይል አቋቁሞ ወደ ስራ መግባቱን ገልጸዋል።

ግብረ ሀይሉም ፈጣን ምላሽ የሚሰጥ የሃኪሞች ቡድን በማዋቀር በመጠለያ ጣቢያዎች የህክምና መስጫ ማእከላት በማቋቋም የህክምናና የልየታ ስራዎች እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል።

ስለ በሽታዎቹ አስከፊነት፣ መከላከያ መንገዶችና መደረግ ስለሚገባ ጥንቃቄ ለተፈናቀሉ ወገኖች ተከታታይ የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት እየተሰጠ መሆኑን ተናግረዋል።


ቡድኑም በመጠለያ ጣቢያዎች ለሚገኙና በአካባቢያቸው ለሚኖሩ 295 ሺህ ሰዎች የአጣዳፊ ተቅማጥና ትውከት መከላከያ ክትባት መስጠቱን ጠቅሰዋል።


በተጨማሪም ለወባ ተጋላጭ የሆኑ አካባቢዎችን በመለየት 180 ሺህ የአልጋ አጎበሮችን  ማሰራጨቱን ጠቁመው የመጸዳጃና የንጽህና መጠበቂያ ቤቶች ግንባታ ስራም መከናወኑን ተናግረዋል ።

የአበርገሌ ወረዳ ፅህፈት ቤት ሃላፊ አቶ አማረ ኪሮስ በበኩላቸው በመጠለያ ጣቢያዎች የሚገኙ ተፈናቃዮች ለጤና ችግር እንዳይጋለጡ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶችን በማሳተፍ በየሳምንቱ የፅዳት ዘመቻ እየተካሄደ መሆኑን ገልጸዋል።

"በተለይም በመጠለያ ጣቢያዎች ውስጥ የሚኖሩ አቅመ ደካሞችንና የሰው ድጋፍ የሚሹ የህብረተሰብ ክፍሎችን በመደገፍ ወጣቶች እያሳዩ ያለው ተነሳሽነት የሚያስመስግን ነው" ብለዋል።

 "በየሳምንቱ የፅዳት ዘመቻ ከማካሄድ ባሻገር ተፈናቃዮች የአተት ክትባቱን እንዲወስዱ የግንዛቤ ማስጨበጥ ስራ ሰርተናል" ያለው ደግሞ በወለህ መጠለያ ጣቢያ የሚገኘው ወጣት አሰፋ ታዘዘ ነው።  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም