በኢትዮጵያ ሁሉን አቀፍ መረጃ በዘላቂነት ለማደራጀት በወሳኝ ኩነት ምዝገባ የህብረተሰቡ ተሳትፎ መጠናከር አለበት- አቶ ተስፋዬ ቤልጂጌ

136

ነሐሴ 4 ቀን 2014 (ኢዜአ) “በኢትዮጵያ ወጥ፣ ተደራሽና ሁሉን አቀፍ መረጃ በዘላቂነት ለማደራጀት በወሳኝ ኩነት ምዝገባ የህብረተሰቡ ተሳትፎ መጠናከር አለበት” ሲሉ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ ቤልጂጌ ተናገሩ።

አምስተኛው አገር አቀፍ የወሳኝ ኩነት ምዝገባና ስታትስቲክስ ቀን በአዲስ አበባ ተከብሯል።

May be an image of 2 people, people sitting and people standing

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ ቤልጂጌ፤ ባስተላለፉት መልእክት የወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ ለፍትሀዊ ውሳኔዎችና ለዜጎች ማህበራዊ አገልግሎት ዋነኛ የመረጃ ምንጭ መሆኑን ገልጸዋል።

ለትክክለኛ የስነ-ህዝብ መረጃ፣ ፍትሃዊ የፖለቲካ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ አገልግሎቶችን ለመስጠትም የወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ የላቀ ሚና እንዳለው አብራርተዋል።

በኢትዮጵያ ወጥ፣ ተደራሽና ሁሉን አቀፍ መረጃ በዘላቂነት ለማደራጀት የወሳኝ ኩነት ምዝገባ የማይተካ ሚና አለው ብለዋል።

መረጃን በጥራት በማከናወን በትክክለኛ መረጃ የተደገፈ፣ የዘመነና የበለጸገ ማህበረሰብ ለመፍጠር ጠቃሚ በመሆኑ ህብረተሰቡ ይህንኑ በመገንዘብ የነቃ ተሳትፎ እንዲያደርግ ጥሪ አስተላልፈዋል።

የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ፣ ለዜጎች ፍትሃዊ የጤና አገልግሎት ተደራሽ የወሳኝ ኩነት ምዝገባ በእጅጉ አስፈላጊ ስለመሆኑ አንስተዋል።

May be an image of 1 person, standing, indoor and text that says "etv etv"

በተለይም ለእናቶችና ህፃናት የጤና ተደራሽነት በማመቻቸት የሞት ምጣኔን ለመቀነስ የሚኖረው ፋይዳ የላቀ መሆኑን ገልጸዋል።

የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ብሩህተስፋ ሙሉጌታ፤ የወሳኝ ኩነት የምዝገባ ሂደት አሁን ላይ አበረታች ውጤት የታየበት መሆኑን ተናግረዋል።

በ16 ሺህ የምዝገባ ጽህፈት ቤቶች ምዝገባው በመካሄድ ላይ መሆኑን ጠቁመው የምዝገባ ሽፋኑ ከጊዜ ወደ ጊዜ መሻሻል እያሳየ መሆኑን ገልፀዋል።

አገር አቀፍ የወሳኝ ኩነት ምዝገባና ስታትስቲክስ እለት ቀን መከበርም ህብረተሰቡ ስለ አገልግሎቱ ይበልጥ ግንዛቤ እንዲኖረው አጋዥ ይሆናል ብለዋል።

እለቱ “የተቀናጀ አገራዊ አመራርና ባለቤትነትን ለማጎልበት የወሳኝ ኩነት ምዝገባና ቫይታል ስታቲስቲክስ ስርዓትን ማጠናከር ሁሉም ሰው እንዲታወቅ ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር ያስችላል” በሚል መሪ ሃሳብ በአገር አቀፍ ደረጃ ለአምስተኛ ጊዜ ተከብሯል።

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ