አምባሳደር ስለሺ በቀለ ከግሪጎሪ ሚክስ ጋር ውጤታማ ውይይት አደረጉ

86

አዲስ አበባ ነሓሴ 03 ቀን 2014 (ኢዜአ) በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ዶ/ር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ ከአሜሪካ ኮንግረስማን እና የአሜሪካ ምክር ቤት የውጭ ግንኙነት ኮሚቴ ሰብሳቢ ግሪጎሪ ሚክስ ጋር ውጤታማ ውይይት አደረጉ።

አምባሳደር ስለሺ በኢትዮጵያ በግጭት እና በተፈጥሮ አደጋ ለተጎዱ አካባቢዎች እየተደረገ ስላለው ሰብዓዊ እርዳታ፣ የሰላም ግንባታ፣ የኢኮኖሚ ዘርፍ እመርታዎች፣ ዴሞክራሲ ግንባታ ፣ ኢትዮጵያ ከአጎዋ ስለታገደችበት፣ HR.6600 እና S.3199 Bills፣ የአልሸባብ የቅርብ ጊዜ ሙከራን እና ሌሎች ጉዳዮች ጋር በተያያዘ ለኮሚቴው ሰብሳቢ ሚክስ ገለፃ አድርገዋል።

የፌዴራል መንግስት በሁሉም ዘርፍ የወሰዳቸው ጉልህ እርምጃዎች ከግምት ውስጥ በማስገባት ሁለቱን ረቂቅ ህጎች ማንሳት እና ኢትዮጵያን ወደ አጎዋ ተጠቃሚነት መመለስ አስፈላጊ መሆኑንም አብራርተዋል።

አምባሳደር ስለሺ አያይዘውም የሀገራቱ የመቶ አመት እና ዘላቂ ግንኙነት በንግድ፣በኢንቨስትመንት፣በአየር ንብረት ለውጥ፣በኢነርጂ፣በሰላምና ደህንነት ላይ ገንቢ ተሳትፎ ማድረግ ተገቢ ነው ብለዋል።

የአሜሪካ ኮንግረስማን እና የአሜሪካ ምክር ቤት የውጭ ግንኙነት ኮሚቴ ሰብሳቢ ግሪጎሪ ሚክስ በበኩላቸው በሰብአዊ አቅርቦት፣ የተኩስ ማቆም፣ የሰላም ግንባታ እና አገራዊ ውይይቶችን በተመለከቱ ጉዳዮች ላይ በተገኘው አወንታዊ መሻሻል አበረታች መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን ታሪካዊ ግንኙነት ወደ ላቀ የንግድና የኢኮኖሚ ትብብር መቀየር እንደሚያስፈልግም አስገንዝበዋል።

በቀጣይም የኢትዮ-አሜሪካ ግንኙነት አሁን ካለው ሁኔታ ባለፈ በሁሉም ዘርፍ እንዲጠናከር ቁርጠኛ መሆናቸውን ለአምባሳደሩ አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም