በ2014 በጀት አመት በፌደራል ፍርድ ቤቶች ከ176 ሺህ በላይ መዛግብት ዕልባት አግኝተዋል

124

ነሐሴ 4 ቀን 2014 (ኢዜአ) በ2014 በጀት አመት በፌዴራል ፍርድ ቤቶች ከ176 ሺህ በላይ መዛግብት ዕልባት ማግኘታቸውን የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት አስታወቀ።

የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት መዓዛ አሸናፊ በፌዴራል ፍርድ ቤቶች እና በፌደራል ዳኞች አስተዳደር ጉባዔ በ2014 በጀት አመት የተከናወኑ ተግባራትንና የ2015 የትኩረት አቅጣጫዎችን አስመልክቶ መግለጫ ሰጥተዋል።

ፕሬዝዳንቷ በመግጫቸው በዳኝነት ነጻነት፣ በአገልግሎት ቅልጥፍና፣ በዳኝነት ተጠያቂነትና ሌሎች በዳኝነት ስርአቱ የተከናወኑ ዋና ዋና ተግባራትና ውጤቶችን ዘርዝረዋል።

በዚህም በ2014 በጀት አመት በአጠቃለይ በፌደራል ፍርድ ቤቶች 176 ሺህ 797 መዛግብት ዕልባት ማግኘታቸውን ገልጸዋል።

ይህም ከ2013 በጀት አመት የመዛግብት አፈጻጸም ጋር ሲነጻጸር ከ5 ሺህ 5 መቶ መዛግብት በላይ ብልጫ አለው ብለዋል።

ፍርድ ቤቶች መዛግብቶችን እልባት ሲሰጡና ሲመረምሩ የፍርድ ቤቶች ፕሬዝዳንቶችን ጨምሮ 392 ዳኞች አማካኝነት ሲሆን የዳኛና መዛግብት ጥምርታን 1 ለ 451 መዛግብት መሆኑን አንስተው አሁንም ጫና እንዳለ አስገንዝበዋል።