የዲጅታል መማሪያ ማዕከላት ብቁ የተማረ የሰው ኃይል ለማፍራት የጎላ አስተዋጽኦ አላቸው

143

ሆሳዕና፤ነሐሴ 3/2014 (ኢዜአ)፡ የዲጅታል መማሪያ ማዕከላት ብቁ የተማረ የሰው ኃይል ለማፍራት ያላቸው አስተዋጽኦ የጎላ መሆኑን የደቡብ ክልል ትምህርት ቢሮ ገለጸ።

ኢትዮ ቴሌኮም በሆሳዕና ከተማ ሄጦ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ያስገነባውን የዲጅታል መማሪያ ማዕከል ዛሬ አስመርቋል።

የደቡብ ክልል ትምህርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ስንታየሁ ስምኦን በርክክብ ሥነ ሥርዓቱ ላይ  እንዳሉት ወቅቱን የሚመጥን  የሰው ኃይል ለማፍራት የዲጅታል መማሪያ ማዕከላት ሚና ከፍተኛ ነው።

የመማር ማስተማር ሂደቱን ቀልጣፋና ተደራሽነት ለማሳደግ የዲጅታል መማሪያ ማዕከላት ማጠናከር ተገቢ መሆኑን አመልክተው፤በኢትዮ ቴሌኮም የተገነቡት ማዕከላት በቀጣይ የሚኖራቸው አስተዋጽኦ የጎላ እንደሚሆን ያላቸውን እምነት  ተናግረዋል።

ማዕከላቱ ለተፈለገው ዓላማ እንዲውሉ ቢሮው አስፈላጊውን ድጋፍና ክትትል እንደሚያድረግ አስታውቀዋል።

በኢትዮ ቴሌኮም የደቡብ ምዕራብ ሪጅን ዳይሬክተር አቶ ሹሜ አብሽሮ በበኩላቸው ኢትዮ ቴሌኮም በዲጅታል ኢኮኖሚ የበቃ የሰው ኃይል ለማፍራት በሀገር አቀፍ ደረጃ ከ44 ሚሊዮን ብር በላይ መድቦ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

66 ትምህርት ቤቶችን በዲጅታል መማሪያ ማዕከላት ለማደራጀት እየተሰራ መሆኑን ጠቁመው በዚህም  ከ140 ሺህ በላይ ተማሪዎችን ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰራ ነው ብለዋል።

ዛሬ በሀዲያ ዞን ሆሳዕና ከተማ በሚገኘው የሄጦ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ግንባታው ተጠናቆ ርክክብ የተደረገለት የዲጅታል መማሪያ ማዕከል አንዱ መሆኑን ጠቁመዋል።

ማዕከሉ ተማሪዎችን ከዲጅታል ኢኮኖሚ ጋር ከማስተዋወቅ ባለፈ ፈጣንና ቀልጣፋ መረጃዎችን እንዲያገኙ እና  በጥናትና ምርምር የተደገፈ ችግር ፈቺ ስራዎች እንዲያከናውኑ እንደሚያስችል አስረድተዋል።

በመርሐ ግብሩ ላይ የደቡብ ክልል ትምህርት ቢሮ፣የሀድያ ዞንና የኢትዮ ቴሌኮም ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎችና የትምህርት ማህበረሰብ አባላት መገኘታቸውን ኢዜአ ከሥፍራው ዘግል።