የተከማቹ የውሃ መያዥ ፕላስቲኮችን መጠን አሳንሶ በቀላሉ ወደ ፋብሪካ በመውሰድ መልሶ ለመጠቀም የሚያግዝ ማሽን ለአምስት ከተሞች ተበረከተ

117

ነሐሴ 3 ቀን 2014/ኢዜአ/የተከማቹ የውሃ መያዥ ፕላስቲኮችን መጠን አሳንሶ በቀላሉ ወደ ፋብሪካ በመውሰድ መልሶ ለመጠቀም የሚያግዝ ማሽን ለአምስት ከተሞች ተበረከተ።

የከተማ ልማትና መሰረተ-ልማት ሚኒስቴር ከተባበሩት መንግሥታት የልማት ፕሮግራም ጋር በመተባበር ለሀዋሳ፣ አዳማ ፣ ባህርዳር ፣ቢሾፍቱና ድሬደዋ ከተሞች ማሽኖቹን አበርክቷል።

በ139 ሺህ ዶላር ወጪ የተደረገባቸው እነዚሁ ማሽኖች የደረቅ ቆሻሻሻ መልሶ ለመጠቀምና ለማስወገድ የሚረዱ መሆኑ ታውቋል።

የከተማ ልማትና መሰረተ ልማት ሚኒስትሯ ጫልቱ ሳኒ፤ ማሽኖቹ በከተሞች የደረቅ ቆሻሻ አጠቃቀምና አወጋገድ ላይ ያለውን ችግር ለመፍታት ያግዛል ብለዋል።

ከተሞች ውብ፣ ፅዱና ለነዋሪዎች ምቹ እንዲሆኑ እየተሰራ ሲሆን በተለይም ፕላስቲኮች የውሃ መውረጃ ቱቦዎችን በመዘርጋት እና አካባቢን በማቆሸሽ ችግር እያስከተሉ መሆኑን ተናግረዋል።

በመሆኑም ነዋሪዎች በከተሞች አካባቢ መሰል ደረቅ ቆሻሻዎችን በመለየት ለዳግም አገልግሎት እንዲውሉ የድርሻቸውን ሊወጡ እንደሚገባ አሳስበዋል።

የቆሻሻ አወጋገድ ስርዓትን በማዘመንና መልሶ ጥቅም ላይ በማዋል ውብ፣ ጽዱና አረንጓዴ የሆኑ ከተሞችን መፍጠር እንደሚያስችል አንስተዋል።

ቆሻሻን መልሶ ተጠቅሞ የተፈጥሮ ማዳበሪያ በማዘጋጀት ለጓሮ አትክልትና ለሌሎች ምርቶች ማዋል እንደሚያስፈልግም አመልክተዋል።

የድጋፉ ተጠቃሚ ከተሞቹ ተወካዮች በበኩላቸው ማሽኖቹ ከዚህ በፊት በፕላስቲክ ቆሻሻ አወጋገድ ላይ ይገጥም የነበረውን ችግር እንደሚቀርፍላቸው ተናግረዋል።

ከአካባቢ ጽዳት በተጨማሪ ማሽኖቹ የስራ ዕድል በመፍጠርና በቴክኖሎጂ ሽግግር ረገድም ጭምር የበኩላቸውን ድርሻ እንዳለቸው ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም