በኢትዮጵያ ኤች አይ ቪ / ኤድስ የማህበረሰብ የጤና ችግር እንዳይሆን የሚያስችሉ ውጤቶች እየታዩ ነው

407

ነሃሴ 3/2014/ኢዜአ/ ኢትዮጵያ ኤች አይ ቪ / ኤድስ በ2030 የማህበረሰብ የጤና ችግር እንዳይሆን የተያዘውን ግብ ለማሳካት የሚያስችሉ ውጤቶችን እያሳየች መሆኑን ጤና ሚኒስቴር ገለጸ።

ኢትዮጵያ ኤች አይ ቪ/ኤድስን በመዋጋት የተገኙትን ውጤቶች ማጠናከርና ኢንፌክሽንና የሞት መጠንን ለመቀነስ የተለያዩ ስትራቴጂዎችን ቀርፃ እየሰራች ትገኛለች።

በጤና ሚኒስቴር የኤች አይቪ መከላከልና መቆጣጠር ቡድን አስተባባሪ ምርቴ ጌታቸው፤ በእቅዱ መሰረት ቫይረሱ በደማቸው ካለባቸው ሰዎች 95 በመቶውን ወደ ምርመራ ማምጣትና ወደ ምርመራ ከመጡት ደግሞ 95 በመቶው የጸረ-ኤች አይ ቪ ህክምና እንዲጀምሩ ማድረግ መሆኑን ያብራራሉ።

ህክምናውን ከጀመሩት መካከል 95 በመቶው በደማቸው የሚገኘውን የቫይረስ መጠን መቀነስ በሚል የተቀመጡ ግቦችን ጠቅሰዋል።

ኤች አይቪ ቫይረስ በደማቸው ካለባቸው ሰዎች መካከል 95 በመቶ ለመለየት ከተቀመጠው ግብ ውስጥ በአሁኑ ወቅት 84 በመቶ ማድረስ መቻሉን አስተባባሪው ገልጸዋል።

የጸረ-ኤች አይቪ ህክምና የሚወስዱ ሰዎች የቫይረስ መጠናቸው 96 በመቶ የሚሆኑ የቫይረስ መጠናቸው በሙያው አጠራር ከአንድ ሺህ ኮፒ በታች ነው ሲሉ ተናግረዋል።

ተመርምረው እራሳቸውን ያወቁ ሰዎች ህክምና እንዲያገኙ አገልግሎት የሚሰጡ የጤና ተቋማትንና የመድሃኒት አቅርቦትን በማስፋት እየተሰራ ይገኛልም ብለዋል።።

የተጠቀሱት ለውጦች እንደ ኤሮፓውያን አቆጣጠር በ2030 ኤች አይ ቪ / ኤድስ የጤና እና የማህበራዊ ችግር እንዳይሆን የተቀመጠውን ግብ ለማሳካት አመላካች ውጤቶች መሆናቸውን ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅት እንደ አገር የኤች አይቪ የስርጭት መጠን ከአንድ በመቶ በታች ቢሆንም በተለያዩ የማህበረሰብ ክፍልና ክልሎች ያለው ስርጭት የተለያየ በመሆኑ የመከላከል ተግባርን ማጠናከር ያስፈልጋል ብለዋል።

ከፍተኛ የስርጭት መጠን ካለባቸው ክልሎች መካከል የጋምቤላ ክልል 3 ነጥብ 9 በመቶ በመያዝ ቀዳሚ መሆኑን መረጃዎች ያሳያሉ።

የክልሉ ምክር ቤት ሴቶችና ህጻናት ማህበራዊ ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ትሁት ቶቤል፤ የስርጭት መጠኑን ለመቀነስና እንደ አገር የተቀመጠውን ግብ ለማሳካት የግንዛቤ ስራዎች እንዲጠናከሩ ክትትል እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል።

በኢትዮጵያ ኤች አይቪ በደማቸው የሚገኝ ጥምረቶች ጥምረት የህዝብ ግንኙነት መምሪያ ሃላፊ አቶ ጌታቸው ጎንፋ፤ ቫይረሱ በደማቸው ውስጥ ያሉ ሰዎችን ማግለልና መድሎ መቀነስ ቢያሳይም  አሁንም መቀጠሉን በ2014 የተደረገ ጥናት ማመላከቱን አንስዋል።

በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ኤች አይቪ በደማቸው ይኖራል ተብሎ ከሚገመቱት 600 ሺህ በላይ ሰዎች  መካከል 60 በመቶ የሚሆኑት ሴቶች መሆናቸውን መረጃዎች ይጠቁማሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም