የጋሞ ጎፋ ዞን አስተዳደር በአዲስ አበባ ዙሪያ ጥቃት ለደረሰባቸው ዜጎች የአንድ ሚሊዮን ብር ድጋፍ ሰጠ

62
አርባምንጭ መስከረም 6/2011 በደቡብ ክልል የጋሞ ጎፋ ዞን አስተዳደር በአዲስ አባባ ዙሪያ በደረሰው ኢሰብአዊ ድርጊት ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች የአንድ ሚሊዮን ብር ድጋፍ ለመስጠት ወሰነ። የዞኑ አስተዳደር ካቢኔ ዛሬ ባደረገው አስቸኳይ ጉባኤ የተፈጸመውን ኢሰብአዊ ድርጊት አውግዟል። የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ኢሳያስ እንድሪያስ ጉዳቱን አስመልክቶ ለመገናኛ ብዙሃን በሰጡት መግለጫ በአዲስ አበባ ዙሪያ የተደራጁ ቡድኖች ባደረሱት ጥቃት በዞኑ ተወላጆች ላይ የህይወትና የንብረት ጉዳት ደርሶባቸዋል። የዞኑ ካቢኔ ዛሬ ባካሄደው አስቸኳይ ስብሰባም በከባድ አካል ጉዳት እየታከሙ ላሉ ተጎጂዎችና ለተፈናቀሉ ቤተሰቦች የሚሆን አንድ ሚሊየን ብር ድጋፍ ለመስጠት መወሰኑንም ገልጸዋል። ጥቃቱ ባስቸኳይ እንዲቆም የጠየቁት አስተዳዳሪው የጋሞ አካባቢ ሁሉም ወረዳ አስተዳዳሪዎችን ያካተተና በሳቸው የሚመራ ከፍተኛ የአመራር ቡድን ጉዳቱ በደረሰበት ሥፍራ በአካል ተገኝቶ ለመጠየቅ መዘጋጀቱንም ተናግረዋል። ለተጎጂዎቹ "አይዞአችሁ እንደርስላችኃለን" የሚል መልዕክት ያስተላለፉት አስተዳዳሪው እነሱን ያስጠለሉ የአዲስ አበባ ከተማና የቡራዩ  ነዋሪዎች ላደረጉት በጎ ስራ ምስጋና አቅርበዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም