በቡራዩና አካባቢው በተፈጠረው ግጭት የተጠረጠሩ ሰዎች በቁጥጥር ስር ዋሉ

100
አዲስ አበባ መስከረም 6/2011 በአዲስ አበባ አቅራቢያ ቡራዩና አካባቢው በተፈጠረው ግጭት የተጠረጠሩ ከ70 በላይ ሰዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ። እስካሁን ባለው መረጃ 23 ሰዎች ሲሞቱ 886 ያህል ዜጎች ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል። የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽነር አቶ አለማየሁ እጅጉ ለኢዜአ እንዳሉት ከሁለት ቀን በፊት የተደራጁ ኃይሎች በቡራዩና አካባቢዋ በሚኖሩ ዜጎች ላይ የህይወት ማጥፋትና የዝርፊያ ወንጀል ፈጽመዋል። በአሁኑ ወቅት የክልሉ ፖሊስ ከፌዴራል ፖሊስና ከመከላከያ ሰራዊት አባላት ጋር በመሆን በአካባቢው ሰላም ለማስፈን በተሰራው ስራ ከ70 በላይ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ገልጸዋል። አጥፊዎችን በቁጥጥር ስር የማዋል ተግባር፣ የአካባቢውን ሰላም በዘላቂነት መመለስና ተፈናቃዮችን ወደቀያቸው የመመለስ ስራ ተጠናክሮ እንደሚሰራም ኮሚሽነሩ ተናግረዋል። በህብረተሰቡ ላይ የህይወት ማጥፋትም ሆነ የዘረፋ ወንጀል የፈጸሙ ተጠርጣሪዎች ማንንም የማይወክሉና ለወንጀል የተደራጁ ናቸው ብለዋል። በአሁኑ ወቅትም የአካባቢው ነዋሪዎች በተፈጠረው ችግር ሳቢያ በስጋት ወደ አዲስ አበባ እየመጡ መሆኑን በመጠቆም ችግሩን ፖሊስ ሙሉ በሙሉ የተቆጣጠረውና የተፈናቀሉትም በፖሊስ ከለላ ስር መሆናቸውን አውቀው ወደቀያቸው እንዲመለሱ ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም