ሆስፒታሉን ሥራ ለማስጀመር የሰው ሃይል እና ግብአት የማሟላት ሥራ እየተሰራ ነው

181

ጎንደር (ነሀሴ) 02/2014 በጎንደር ከተማ በ140 ሚሊዮን ብር ወጪ የተገነባውን አይራ አጠቃላይ ሆስፒታል ሥራ ለማስጀመር የሰው ሃይልና ግብአት የማሟላት ሥራ እየተከናወነ መሆኑን የአማራ ክልል ጤና ቢሮ አስታወቀ።

በክልሉ የሚገኙ የጤና ባለሙያዎችና የሥራ ሃላፊዎች ዛሬ በሆስፒታሉ ቅጥር ግቢ ችግኝ በመትከል አረንጓዴ አሻራቸውን አሳርፈዋል።

የቢሮው ሃላፊ ዶክተር መልካሙ አብቴ በችግኝ ተከላው ላይ እንዳሉት የሆስፒታሉ ግንባታ በሥራ ተቋራጮች መቀያየር ምክንያት ከ10 ዓመት በላይ ሳይጠናቀቅ ቆይቷል።

ይሁን እንጂ ባለፉት ሁለት ዓመታት የክልሉ መንግስት ችግሩን ገምግሞ የማስተካከያ እርምጃ በመውሰዱ የሕንጻ ግንባታ ሥራው ሊጠናቀቅ መቻሉን ገልጸዋል።

ሃላፊው እንዳሉት በአሁኑ ወቅት ለሆስፒታሉ የባለሙያዎች ቅጥር በመፈጸምና የሕክምና ግብአቶችን በማሟላት በመጪው መስከረም ወር ላይ ሥራ ለማስጀመር እየተሰራ ነው።

“ዛሬ በአረንጓዴ አሻራ የተካሄደው የችግኝ ተከላም ለሆስፒታሉ ታካሚዎች ጽዱና ውብ አካባቢ ለመፍጠር ከወዲሁ ያለመ ነው” ብለዋል።

ሆስፒታሉ 400 የሚጠጉ የሕሙማን አልጋዎች እንደሚኖሩትና ለጎንደርና አካባቢው ማህበረሰብ ተገቢ የሕክምና አገልገሎት ለመስጠት እንደሚያስችል የገለጹት ደግሞ የጎንደር ከተማ ጤና መምሪያ ሃላፊ አቶ በለጠ ፈንቴ ናቸው።

እንደእሳቸው ገለጻ ሆስፒታሉ አገልግሎት መስጠት ሲጀመር ከ2 ሚሊዮን በላይ ሰዎችን ተጠቃሚ ያደርጋል።

ሆስፒታሉን በግብዓት ለማሟላት በተደረገ ጥረት 200 ዘመናዊ የሕሙማን አልጋዎች ከውጪ ለጋሽ ድርጅቶች በእርዳታ ለማግኘት መቻሉን ገልጸዋል።

የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ጤና መምሪያ ምክትል ሃላፊ ወይዘሮ ምሳ ታረቀኝ በበኩላቸው እንዳሉት፣ ሆስፒታሉ በቀደሞ ሰሜን ጎንደር ሥር የነበሩ ሦስት ዞኖችን እንዲያገለግል ታስቦ የተገነባ ነው።

“የሆስፒታሉ መገንባት የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታል ከተለያዩ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታሎች በሪፈር በሚላኩለት ሕሙማን ሲፈጠርበት የነበረውን መጨናነቅ ለመቀነስ ያስችላል” ብለዋል።

“ሆስፒታሉን በአዲሱ ዓመት መጀመሪያ ወደሥራ በማስገባት ለጎንደርና አካባቢው ማህበረሰብ አዲስ ገጸ በረከት ይሆናል” ሲሉም ገልጸዋል።

በአይራ አጠቃላይ ሆስታል በተካሄደ የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሀ ግብር ከ6ሺህ በላይ ሀገር በቀል ችግኞች መተከላቸውን ለማወቅ ተችሏል።