በክረምቱ የማጠናከሪያ ትምህርት እየተማርንና እያነበብን ተጨማሪ እውቀት እያገኘንበት ነው- ተማሪዎች

125

ነሐሴ 2 ቀን 2014 (ኢዜአ) በክረምቱ የማጠናከሪያ ትምህርት እየተማርንና እያነበብን ተጨማሪ እውቀት እያገኘንበት ነው ሲሉ በአዲስ አበባ ኢዜአ ያነጋገራቸው ተማሪዎች ገለጹ።

በአዲስ አበባ እየተከናወኑ ካሉ የበጎ ፈቃድ አገልግሎቶች መካከል የክረምት የማጠናከሪያ ትምህርት አንዱ ነው ።

በመሆኑም “በጎነት ለዘላቂ አብሮነትና ወንድማማችነት” በሚል መሪ ሀሳብ ከሰኔ 11 ቀን 2014 ዓ.ም ጀምሮ በአዲስ አበባ ለተማሪዎች የክረምት የማጠናከሪያ ትምህርት በመሰጠት ላይ ይገኛል።

በዚሁ አገልግሎት በመማር ላይ የሚገኙ ተማሪዎችን የኢዜአ ሪፖርተር በአዲስ ብርሃን  እና ድል በትግል የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በመገኘት አነጋግሯል።

በድል በትግል የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ያገኘናቸው ተማሪ ሀምዛ ተካ እና ተማሪ ሄለን ካሳሁን የክረምቱ የማጠናከሪያ ትምህርት ጥሩ እውቀት እያገኘንበት ያለ መልካም አጋጣሚ ነው ብለዋል።

በአዲስ ብርሃን  የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ያገኘናት ተማሪ ከነዓን  መስፍን በበኩሏ የክረምቱ የማጠናከሪያ ትምህርት እየተማርንና እያነበብን ተጨማሪ እውቀት እያገኘንበት ነው ብላለች።

ድል በትግል የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት  የሚያስተምረው መምህር ተክለመድህን ተስፋዬ፤ በበጎፈቃደኝነት ዘንድሮ ለአራተኛ ጊዜ መሳተፉን ገልጾ እውቀቱን ለተውልዱ በማካፈሉ ደስተኛ መሆኑን ተናግሯል።

በአዲስ ብርሀን የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ለሰባተኛና ለስምንተኛ ክፍል ተማሪዎች ኬምስትሪ እያስተማረ ያገኘነው መምህር አረጋኸኝ እንግዳ፤ የክረምቱ ትምህርት ተማሪዎች እውቀታቸውን እንዲያጎለብቱ ጥሩ መሰረት እየጣለ መሆኑን ተናግሯል።

በአዲስ አበባ የኅብረተሰብ ተሳትፎና ማስተባበሪያ ኮሚሽን ኮሚሽነር አስፋው ተክሌ፤ በክረምቱ 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ወጣቶችን በማሳተፍ ትምህርትን ጨምሮ ህብረተሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል።

በመዲናዋ ለ33 ሺህ የአንደኛ እና የሁለተኛ ደረጃ  ትምህርት ቤት ተማሪዎች የክረምት የማጠናከሪያ ትምህርት እንዲሁም ለ2 ሺህ ተማሪዎች የክህሎት ስልጠና እየተሰጠ መሆኑን ተናግረዋል ።