የወጣቶች የበጎ ፍቃድ ስልጠና ለሀገር ሰላምና አንድነት ጉልህ ሚና እያበረከተ ነው-አምባሳደር እሸቱ ደሴ

133

ጅማ፣ ነሐሴ 1/2014 (ኢዜአ) የወጣቶች የበጎ ፍቃድ ስልጠና ለሀገር ሰለምና አንድነት ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን የሰላም ሚኒስትር አማካሪ አምባሳደር እሸቱ ደሴ ተናገሩ።

በሰላም ሚኒስቴር አስተባባሪነት በጅማ ዩኒቨርሲቲ ለ30 ቀናት የብሔራዊ የማህበረሰብ በጎ ፍቃድ አገልግሎት ስልጠና የወሰዱ 1 ሺህ 500 ወጣቶች ዛሬ ተመርቀዋል።

በምረቃ ሥነ ስርዓቱ ላይ  የተገኙት አምባሳደር እሸቱ ደሴ እንዳሉት  የወጣቶች የበጎ ፍቃድ ስልጠና ለሀገር ሰላምና አንድነት ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው።

የበጎ ፍቃድ ማህበረሰብ ልማት አገልግሎት በተለያዩ ቦታዎች ላይ  የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ሰጪ ወጣቶችን እያፈራ መሆኑን አመልክተዋል።

ወጣቶቹ የተለያዩ ባህልና ቋንቋን በመማር  የሰላም አምባሳደር በመሆን እያገለገሉ መሆኑን አመልክተው፤ ወደ ተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች በመሄድ የበጎ ፍቃድ ስራዎችን እየከወኑ መሆኑን ተናግረዋል።

ይህም ከጊዜ ወደ ጊዜ በሀገር ሰላምና አንድነት ላይ የራሱን በጎ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን ጠቁመዋል።

የጅማ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ጀማል አባፊጣ በበኩላቸው  ሀገር  ሰላምን መሰረት ባደረገ ውይይት፣ ንግግርና መግባባት መገንባት አለባት ብለዋል።

 በተለይም ወጣቶች የንግግርና ውይይት ባህልን በማዳበር በችግር ወቅት በጋራ መቆምና መሻገር የሚቻልበትን ሁኔታ  ሊገነዘቡ እንደሚገባ ገልጸዋል።

ፕሬዚዳንቱ አክለውም ተመራቂ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ሰጭ ወጣቶች ሰላምን መርህ ባደረገ መልኩ በሚሰማሩብት አካባቢ ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ መክረዋል።

ባለፉት ሶስት ዙሮች ሰልጥነው የተመረቁትን  የብሔራዊ በጎ ፍቃድ ማህበረሰብ አገልግሎት ጨምሮ  በአራት ዙር ሥልጠና  ከ9 ሺህ በላይ ወጣቶች በጅማ ዩኒቨርሲቲ ተመርቀዋል።

ዛሬ ከተመረቁ የብሔራዊ በጎ ፍቃድ ማህበረሰብ አገልግሎት ሰልጣኝ ወጣቶች መካከል  ወጣት በጋሻው ባታኖ በስልጠናው በርካታ የተግባቦት፣ የሥነ ምግባርና የበጎ ፍቃድ እውቀቶችን ማግኘቱን ተናግሯል።

''ለሰው ልጅ ሰብዓዊ ክብር መስጠት፣ የኔ እገዛ ሲያስፈልጋቸው ማገዝና መተባበር ምን ያህል የስብዕና ልዕልና እንዳለው የተረዳሁበት ቆይታ ነበር'' ብሏል።

ወጣት ዘመን ክቡር በበኩሏ በጅማ ዩኒቨርስቲ በነበራት ቆይታ በተግባር የተደገፈ የበጎነት ስራዎችን ከመስራት ባለፈ ጠቃሚ ትምህርቶችን ማግኘቷን ተናግራለች።

''ስልጠናው ለህይወቴ ይጠቅመኛል ከዚያም ባለፈ ህብረተሰቡን ለማገልገል የሚያስችለኝን ግንዛቤ ያገኘሁበት በመሆኑ እድለኛ'' ብላለች።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም