የጋራ ችግሮችን በመተጋገዝ መፍታት ይገባል- አቶ ገብረመስቀል ጫላ

140

ሶዶ፣ነሐሴ 01/2014 (ኢዜአ)፡ የጋራ ችግሮችን በመተጋገዝ የመፍታት ባህልን ማጎልበት እንደሚገባ የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስትር አቶ ገብረመስቀል ጫላ ተናገሩ።

የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴርና ተጠሪ ተቋማት አመራሮችና ሰራተኞች  በወላይታ ሶዶ ከተማ የአቅመ ደካሞችን ቤት እድሳት ዛሬ አስጀምረዋል።

በመተጋገዝ መርህ የጋራ ችግሮችን በጋራ የመፍታት ባህል ሊጎለብት እንደሚገባ ያመለከቱት ሚንስትሩ፤  ባህሉን በማጠናከር በተለያዩ የበጎ ፈቃድ አገልግሎቶች መሳተፍ ይገባል ብለዋል።

”በአንድነት መቆም ለጋራ ችግሮች የጋራ መፍትሔ ለማምጣት ይረዳል” ያሉት ሚኒስትሩ፤ አንድነትን በማጠናከር የኢትዮጵያን ብልፅግና እውን ማድረግ እንደሚገባ ተናግረዋል።

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱና ተጠሪ ተቃማት ዛሬ በወላይታ ሶዶ ከተማ ያስጀመሩት የአራት  የአቅመ ደካሞች የመኖሪያ ቤት እድሳት የዚሁ ማሳያ መሆኑን ያመለከቱት ሚኒስትሩ፤ የቤቶቹ ግንባታ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ግብዓቶች ልማት ዋና ስራ አስፈፃሚ ወይዘሮ የሺመቤት ነጋሽ በበኩላቸው በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት 37 የአቅመ ደካሞች ቤት መገንባታቸውን ተናግረዋል።

 በበጀት ዓመቱ 16 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ወጪ በማውጣት የተፈጥሮ አደጋ እና የሰላም እጦት በተከሰተባቸው የተለያዩ አካባቢዎች ማህበራዊ ድጋፍ መደረጉን ገልጸዋል።

ለአቅመ ደካሞችና አረጋውያን የመኖሪያ ቤት እድሳት ለማካሄድ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ለወሰደው ቁርጠኝነት ምስጋና ያቀረቡት ደግሞ የወላይታ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አክሊሉ ለማ ናችው።

በዞኑ የደም ልገሳና የአቅመ ደካሞች መኖሪያ ቤት እድሳት ጨምሮ በርካታ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሥራዎች በመከናወን ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ይህም የእርስ በርስ የመተጋገዝ ባህልን በማጎልበት የማህበራዊ ትስስርን እያጠናከረ መሆኑን አስረድተዋል።

የተሰሩ የበጎ ፈቃድ አገልግሎቶች   ከመንግስትና ህዝብ ሊወጣ የሚችል ሀብት ከማዳን ባለፈ የህብረተሰቡን የልማት ጥያቄ የመለሰ መሆኑን አስረድተዋል።

የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴርና ተጠሪ ተቋማት ዛሬ ጠዋት በወላይታ ሶዶ የችግኝ ተከላ ማከናወናቸው ይታወቃል።