በኢትዮጵያ እውቅና የሌለውን ዲጂታል መገበያያ ገንዘብ ለመጠቀም ከሚንቀሳቅሱ አካላት ህብረተሰቡ እራሱን መጠበቅ አለበት

415

ነሀሴ 01/2014 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ እውቅና የሌለውን ምናባዊ ንብረት ወይም ዲጂታል መገበያያ ገንዘብ ለመጠቀም ከሚንቀሳቅሱ አካላት ህብረተሰቡ እራሱን መጠበቅ እንዳለበት የፋይናንስ ደሕንነት አገልግሎት አሳሰበ።

አገር ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ ባለው የጥቁር ገበያ የሚሳተፉ አካላትን ለይቶ እርምጃ እንዲወሰድባቸው በማድረግ ሂደትም አገልግሎቱ የበኩሉን አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑም ተገልጿል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በዓለም ዙሪያ ምናባዊ ንብረት ወይም ዲጂታል መገበያያ ገንዘብ ዝውውር እየተበራከተ መምጣቱ ይስተዋላል፡፡

በኢትዮጵያም በተወሰነ መልኩ ስራ ላይ በመዋሉ ግለሰቦች ተሳታፊ መሆናቸውን የፋይናንስ ደሕንነት አገልግሎት አስታውቋል።

የአገልግሎቱ ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ እንዳለ አሰፋ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የዲጂታል ገንዝብ እንቅስቃሴ ተበራክቷል።

በተለይም ‘ቢትኮይን’ እና ‘ክሪፕቶከረንሲ’ የተሰኙ የ’ኦን ላይን’ ዲጂታል ገንዘብ ዝውውሮች መኖራቸውን ጠቁመዋል።

ምንም እንኳን ዓለም ወደ ዲጂታል አካሄድ እየተቀየረች ቢሆንም እነዚህን ሁኔታዎች መከታተልና መቆጣጠር የሚያስችሉ ሕጎች ያስፈልጋሉ ብለዋል።

የዲጂታል ገንዘብ አንቅሳቃሾችን መቆጣጠር የሚያስችሉ ሕጋዊ ሁኔታዎች እስከሚዘጋጁ ድረስ ለጊዜው ሕዝቡ አስፈላጊውን ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለበት አሳስበዋል።

በተጨማሪም በኢትዮጵያ የንግድ ሕግ ውስጥ ‘ፒራሚድ’ የተሰኘ የንግድ አካሄድ ስለማይፈቀድ ይህንን በ’ኦን ላይን’ መስራት ወንጀል መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በቅርቡም እውቅና የሌለው ‘ፊያስ 777′ የተባለ የ’ኦን ላይን’ ገንዘብ አዘዋዋሪ የፒራሚድ ንግድ ሕግን ሲያከናውን ቆይቶ ብዙዎችን ለኪሳራ ዳርጓል ብለዋል፡፡

እንደ አቶ እንዳለ ገለጻ፤ የፋይናንስ ደሕንነት አገልግሎት በወንጀል የተገኘ ገንዘብን ሕጋዊ አስመስሎ የሚያቀርቡ፣ ሽብርተኝነትን በገንዘብ የሚደግፉና የጅምላ ጨራሽ መሳሪያዎች ብዜትን በገንዘብ የሚረዱ አካላትን ተከታተሎ ለሚመለከታቸው አካላት ሪፖርት ያቀርባል፡፡

አገልግሎቱ ይህንን ስራውን ውጤታማ ለማድረግ አልሞ ከተለያዩ አካላት ጋር በመሆን ትልልቅ ወንጀሎችን መለየት የሚያስችል ጥናት እያካሄደ መሆኑን አንስተዋል።

በቀጣይ ዓመት ሊጠናቀቅ የሚችለው ይሄው ጥናት በቀዳሚነት ከገንዘብ ጋር በተያያዘ ትልቅ ጉዳት ሊያደርሱ የሚችሉ ወንጀሎችን ለመከላከል ትኩረት በማድረጉ ትልቅ ፋይዳው የጎላ ነው ብለዋል፡፡

በተመሳሳይ አገልግሎቱ የወጪ አገር ገንዘቦችን በጥቁር ገበያ የሚመነዝሩ አካላትን ተጠያቂ የማድረግ ስራም በስፋት እያከናወነ መሆኑን አንስተዋል፡፡

የጥቁር ገበያ የገንዘብ ምንዛሬ በአገር ላይ ከፍተኛ ጉዳት ከሚያስከትሉ ሕገ ወጥ ገንዘብ እንቅስቃሴዎች ውስጥ በዋናነት የሚጠቀስ ነውም ብለዋል።

በዚህ መንገድ የሚያልፉ ገንዘቦች ምንጫቸው ሙስና፣ የኮንትሮባንድ ንግድ፣ ታክስ ማጭበርበር፣ ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር፣ ሕገ ወጥ ሓዋላ፣ አደንዛዥ ዕጽ ዝውውርና ሕገ ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር መሆናቸውንም ተናግረዋል።

አገልግሎቱ በዚህ ዙሪያ የሚንቀሳቁ አካላትን ተጠያቂ ለማድረግ አስፈላጊ መረጃዎችን ለፖሊስ ተደራሽ እያደረገና በዚህም ውጤቶች እየተገኙ መሆኑን ገልጸዋል።