የአሉቶ ላንጋኖ የእንፋሎት ሀይልና አይሻ ሁለት የንፋስ ሀይል ማመንጫዎች ተጨማሪ ኃይል ማመንጨት ይጀምራሉ

269

ነሀሴ 01/2014 (ኢዜአ)የአሉቶ ላንጋኖ የእንፋሎት ሀይልና አይሻ ሁለት የንፋስ ሀይል ማመንጫዎች ጨምሮ ሌሎች የተለያዩ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ጣቢያዎች በተያዘው ዓመት ተጨማሪ ኃይል ማመንጨት እንደሚጀምሩ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አስታወቀ።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የኮርፖሬት ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር ሞገስ መኮንን ለኢዜአ እንዳሉት፤ በኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ፍላጎቱ በየጊዜው እየጨመረ መጥቷል፡፡

በኢትዮጵያ የከተሞች መስፋፋትና አዳዲስ የስራ ዕድል ፈጠራዎች ከፍተኛ ኃይል የሚፈልጉ መሆናቸውን ተከትሎ  በየዓመቱ ፍላጎቱ እያደገ መምጣቱን ገልጸዋል።

በመሆኑም የኤሌክትሪክ ኃይል ፍላጎቱንና ስብጥሩን ለማመጣጠን በተያዘው በጀት ዓመት የተለያዩ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ጣቢያዎች ተጨማሪ ኃይል ማመንጨት ይጀምራሉ ብለዋል፡፡

በዚህም በ2015 በጀት ዓመት የአሉቶ ላንጋኖ የእንፋሎት ሀይል ማመንጫና የአይሻ ሁለት የንፋስ ሀይል ማመንጫዎችና ሌሎቹም ኃይል ማምረት ይጀምራሉ ብለዋል፡፡

''ከአሉቶ ላንጋኖ የእንፋሎት ሀይልና አይሻ ሁለት የንፋስ ሀይል ማመንጫዎች እስከ 180 ሜጋ ዋት ተጨማሪ የኤሌክትሪክ ኃይል ወደ ብሔራዊ ቋት እናስገባለን'' ብለዋል፡፡

የኮይሻ የውሃ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት አፈፃፀም 52 ነጥብ 8 በመቶ፣ የአይሻ ሁለት የንፋስ ኃይል ማመንጫ ደግሞ ከ80 በመቶ በላይ መድረሳቸውንም ተናግረዋል።

አጠቃላይ የግንባታ ሂደቱ ከ 31 በመቶ በላይ የደረሰው የአሰላ የንፋስ ኃይል ማመንጫ በዘንድሮው ዓመት ይጠናቀቃል ተብሎ እንደሚጠበቅም ገልጸዋል፡፡

በአዲስ አበባና ዙሪያዋ ባሉ ስምንት ማከፋፈያ ጣቢያዎች ሲካሄድ የነበረው የአቅም ማሳደጊያና ማስፋፊያ ስራ ሙሉ በሙሉ ተጠናቋልም ብለዋል፡፡

ከ80 በመቶ በላይ የሚሆነው ሀይል የሚመነጨው ከውሃ ሃብት መሆኑን የገለጹት አቶ ሞገስ፤ የሀይል ስብጥሩን ለማመጣጠን የግል ባለሃብቱን በማሳተፍ ለውጥ ማስመዝገብ ተችሏል ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም