የቴክኖሎጂ ዕውቀት ያላቸው ወጣቶች ሀሳባቸውን ወደ ተግባር መቀየር የሚችሉበት የገንዘብና የቴክኒክ ድጋፍ ይደረጋል

260

ነሀሴ 01/2014 (ኢዜአ) የዲጅታል ቴክኖሎጂ ዕውቀትና ክህሎት ያላቸው ወጣቶች ሀሳባቸውን ወደ ተግባር መቀየር እንዲችሉ የገንዘብና የቴክኒክ ድጋፍ እያደረገ መሆኑን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ገለጸ፡፡

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ሁሪያ አሊ ለኢዜአ እንዳሉት፤ የቴክኖሎጂ መሰረተ ልማት ግንባታ በትኩረት እየተሰራ ነው።

የሚገነቡ የቴክኖሎጂ መሰረተ ልማቶችን ተረድቶ መጠቀምና አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን መፍጠር የሚችል የዲጅታል ማህበረሰብ መፍጠር ቅድሚያ የሚሰጠው ተግባር ነው ብለዋል።

በዚህም ወጣቶች የዲጅታል እውቀት እንዲኖራቸው ለማድረግ በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችና ዩኒቨርሲቲዎች በስርዓተ ትምህርት ተካቶ እንዲሰጥ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

በተጨማሪም የዲጅታል ዕውቀትና ክህሎት የሚያስፈልጋቸው ወጣቶች ባሉበት ቦታ ሆነው መማር የሚችሉበት የኦንላይን ትምህርት እየተሰጠ መሆኑን ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ ወጣቶች የዲጅታል ቴክኖሎጂ ዕውቀትና ክህሎት እንዲኖራቸው ማድረግ ብቻ ሳይሆን ያገኙትን ዕውቀት ወደ ተግባር የሚቀይሩበት ዕድል መፍጠር ይገባል ብለዋል።

በዚህም ለአገር ኢኮኖሚ ዕድገት አስተዋጽኦ የሚያደርግ ሀሳብ ያላቸው ወጣቶች የሚለዩበት አሰራር መዘርጋቱን ተናግረዋል።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ከዓለም ባንክ ባገኘው ብድር አማካኝነት ጠቃሚ ሃሳብ ያቀረቡ የፈጠራ ባለሙያዎችን ያበረታታል ብለዋል።

የዲጂታል ቴክኖሎጂ የፈጠራ ሀሳቦች ለሀገርና ህዝብ ከሚሰጡት ጥቅም አኳያ በውድድር ተለይተው ወደ ተግባር ለመቀየር ከሚያስፈልገው ወጭ ግማሹ በሚኒስቴሩ እንዲሸፈን የሚደረግበት አሰራር መኖሩን ጠቁመዋል።

የዲጅታል ቴክኖሎጂ ዕውቀት ያላቸው ወጣቶች ሀሳባቸውን ወደ ተግባር ቀይረው ለአገርና ህዝብ ጥቅም እንዲያውሉት የሚደረገው የገንዘብና የቴክኒክ ድጋፈ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ገልጸዋል።