የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴርና ተጠሪ ተቋማት በወላይታ ሶዶ ችግኝ ተከሉ

ሶዶ፣ነሀሴ 01/2014 (ኢዜአ) የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴርና ተጠሪ ተቋማት ሰራተኞችና አመራሮች በወላይታ ሶዶ ችግኝ በመትከል አረንጓዴ አሻራቸውን አኖሩ ።

የተቋማቱ ሰራተኞችና አመራሮች በወላይታ ሶዶ አደጋ ስጋት አመራር በተለምዶ የእህል ዲፖ ግቢ እና በግብርና ኮሌጅ መካከል በሚገኘው ለጎርፍ ተጋላጭ በሆኑ ቦታዎች ላይ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር አካሂደዋል።

የኢፌዴሪ ንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር ሚኒስትር ገብረመስቀል ጫላ በዚሁ ጊዜ እንደተናገሩት ችግኝ መንከባከብ እንደ መትከሉ ስራ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል።

ምርታማነትን በመጨመር የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥና የድህነት ቀንበር ለመስበር በተለይ ለምግብነት የሚውሉ ችግኞች መትከል ጉልህ ሚና እንዳለው ተናግረዋል።

ከውጪ የሚገቡ የተለያዩ ምርቶች እዚሁ ሀገራችን በማምረት ምርቱን መተካት የሚያስችል በመሆኑ ሁሉም ዜጎች ኃላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል ብለዋል።

በመሆኑም ሚኒስቴሩና ተጠሪ ተቋማቱ ችግኞቹን ከመትከል ባለፈ በመንከባከብ ሃላፊነታቸውን እንደሚወጡም አስረድተዋል ።

የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ግብዓቶች ልማት ዋና ስራ አስፈፃሚ ወይዘሮ የሺመቤት ነጋሽ በበኩላቸው በሀገሪቱ የሚስተዋሉ ችግሮችን መቅረፍ በመንግስት አቅም ብቻ የሚቻል አለመሆኑን ገልጸዋል።

ችግኝ ተከላውም የህብረተሰቡን የምግብ ዋስትና የሚያረጋግጥ በመሆኑ እነዚህና መሠል የተለያዩ ማህበራዊ ድጋፎችን ማድረግ ይገባል ብለዋል።

በንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴርና ተጠሪ ተቋማት ከችግኝ ተከላው ቀጥለው የአቅመ ደካሞች ቤት የማደስ ስራ ያስጀምራሉ ተብሎ ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም