ኢትዮጵያ የአለም ከ20 አመት በታች አትሌቲክስ ሻምፒዮና በ12 ሜዳሊያዎች 3ኛ ሆና አጠናቀቀች

526

ነሐሴ 1 ቀን 2014 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ ኮሎምቢያ ካሊ በተካሄደው የአለም ከ20 አመት በታች አትሌቲክስ ሻምፒዮና 6 የወርቅ ፣5 የብር እና 1 ነሃስ በድምሩ 12 ሜዳሊያዎች በማግኘት ከአለም 3ኛ ሆና አጠናቃለች::

ኢትዮጵያ በሻምፒዮናው ማጠናቀቂያ እለት ብቻ አራት ወርቅ እና ሁለት የብር ሜዳሊያዎችን ማሳካት ችላለች::

በዚህም 19ኛውን የአለም ከ20 አመት በታች አትሌቲክስ ሻምፒዮና በ6 የወርቅ ፣5 የብር እና 1 ነሃስ በድምሩ 12 ሜዳሊያዎች በማግኘት ከአለም ሶስተኛ ፣ከአፍሪካ ደግሞ 1ኛ በመሆን ጨርሳለች::

አሜሪካ በ7 የወርቅ፣4 የብርና 4የነሐስ በድምሩ 15 ሜዳሊያዎችን በመሰብሰብ የሜዳሊያ ሰንጠረዡን በበላይነት ፈፅማለች::ጃማይካ በ6 ወርቅ፣7 የብር እና 3 የነሐስ በድምሩ በ16 ሜዳሊያ ከአሜሪካ ቀጥላ ሁለተኛ ሆናለች።

ኬንያ 3 ወርቅ፣3 የብር እና 4 የነሐስ በድምሩ በ10 ሜዳሊያ አራተኛ ደረጃ ስታገኝ ፣ሌላኛዋ የአፍሪካ ሃገር ደቡብ አፍሪካ 2 የወርቅ 1 ብር እና 2 ነሃስ በድምሩ 5 ሜዳሊያ በመሰብሰብ 5ኛው በመሆን ከአንድ እስከ አምስት ያለውን ደረጃ ይዘው አጠናቀዋል።

ኢትዮጵያ በኮሎምቢያ ካሊ ላለፉት ስድስት ተከታታይ ቀናት ሲካሄድ በሰነበተው የዓለም ከ20 ዓመት በታች አትሌቲክስ ሻምፒዮና በ19 አትሌቶች ተወክላለች::

አትሌቶቹ በሁለቱም ፆታ በ10 የውድድር ተግባራት ብቻ በመሳተፍ አንፀባራቂ ድል ማስመዝገባቸው ተገልጿል::