በኦሮሚያ ክልል በወጣቶች ከ1 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር በላይ የሚገመቱ የበጎ ፍቃድ ስራዎች መከናወናቸው ተገለጸ

73

አዳማ፤ ሐምሌ 30/2014(ኢዜአ) በክልሉ በወጣቶች አደረጃጀት ከ1 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር በላይ የሚገመቱ የተለያዩ የበጎ ፍቃድ ስራዎች መከናወናቸውን የኦሮሚያ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ገለጸ።

ከ300 ሚሊዮን በላይ ችግኞች  መተከላቸውም ተመልክቷል።

ከ1 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር በላይ የሚገመቱ የበጎ ፍቃድ አገልግሎቶቹ የተከናወኑት ባለፈው የበጋ ወቅት በወጣቶች አደረጃጀት የዜግነት አገልግሎት ፕሮግራም መሆኑን የቢሮው ምክትል ሃላፊ አቶ ከድር እንዳልካቸው ለኢዜአ ተናግረዋል።

ከተከናወኑት የበጎ ፍቃድ ስራዎች መካከል ከክልሉ እስከ ከተማና ገጠር ቀበሌዎች ድረስ የአቅመ ደካሞችን ቤት ጥገናና ግንባታ፣ የደም ልገሳ እንደሚገኙበት ጠቅሰዋል።

እንዲሁም 174 ሺህ ለሚሆኑ ወጣቶች በተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃ የስራ ዕድል መፈጠሩንም ጠቁመዋል።

በተለይ በወጣቶች ዘንድ የሚስተዋለው የስራ ጠባቂነት አስተሳሰብ እንዲለወጥና የስራ ፈጠራ ባህላችን እንዲጎለብት ለ1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ወጣቶች የክህሎትና ግንዛቤ ማስጨበጫ አቅም ግንባታ ስልጠና መሰጠቱንም ገልጸዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ በአራተኛው  ዙር የአረንጓዴ አሻራ ፕሮግራም በክልሉ ወጣቶች አደረጃጀት ለመትከል ከታቀደው ከ500 ሚሊዮን በላይ ችግኞችን ውስጥ እስካሁንም  ለምግብና ለደን ልማት የሚውሉ ከ300 ሚሊዮን የሚበልጡ መተከላቸውን አቶ ከድር  አመልክተዋል።

ዕቅዱን ለማሳካት ፕሮግራሙን አጠናክረው መቀጠላቸውን ገልጸው፤ በተያዘው ክረምት ከ1ሺህ 200 በላይ የአቅም ደካሞች ቤት ማደስና ግንባታ መከናወኑን አስረድተዋል።

1ሺህ 560 የደም ዩኒቶች መሰብሰቡን አመልክተው፤ የደም ልገሳ፣ የአካባቢ ጥበቃ፣ ፅዳትና  የተተከሉትን ችግኞች የመንከባከብ ስራ በቀጣዩ በጋም ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

ወጣቶቹ የበጎ ፈቃድ አገልግሎቱን ካከናወኑባቸው ከተሞች መካከል የአዳማ ከተማ ወጣቶችና ስፖርት ጽሕፈት ቤት ሃላፊ አቶ ሞአታ አብደላ እንደገለጹት በከተማዋ በክረምቱ በወጣቶች የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ከ250ሺህ በላይ ችግኞች ለመትከል ታቅዶ 102 ሺህ ተተክሏል።

12 የአቅመ ደካማ ቤቶችን ለማደስና ለመስረት አቅደናል ያሉት ሃላፊው፤ እስካሁንም አምስት ቤቶችን አጠናቀው  ማስረከባቸውን አስታውቀዋል።

“እኛ በዜግነት አገልግሎት ባለን ጉልበትና አቅም ህብረተሰቡ ለማገልገል እየሰራን ነው” ያለው ደግሞ የከተማዋ ነዋሪ ወጣት ታዬ ተሊላ ነው።

ተደራጅተው የበጎ አድራጎት ስራውን  በመቀጠል የአካባቢያቸውን  ሰላም ከመጠበቅ ባለፈ በአረንጓዴ አሻራ፣ የማጠናከሪያ ትምህርት በመስጠት፣ ደም በመለገስ፣ የአቅመ ደካሞች ቤት በማደስ የድርሻቸውን እየተወጡ መሆናቸውን ተናግሯል።