በኦሮሚያ ክልል በድርቅና ሌሎች ሰው ሰራሽ አደጋዎች ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎች ሰብአዊ ድጋፍ እየተደረገ ነው

102

ሀምሌ 30/2014/ኢዜአ/ በኦሮሚያ ክልል በድርቅና ሌሎች ሰው ሰራሽ አደጋዎች ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎች ሰብአዊ ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን የቡሳ ጎኖፋ ኦሮሚያ አስታወቀ።

የኦሮሚያ ክልል አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን የሚል መጠሪያ የነበረው ተቋም አሁን ላይ የቡሳ ጎኖፋ ኦሮሚያ በሚል አዲስ ስያሜ ሥራውን በማከናወን ላይ ይገኛል።

በዚህም በክልሉ በተለያዩ ምክንያቶች በችግር ላይ ለሚገኙ ወገኖች የተጠናከረ ሰብአዊ ድጋፍ እያደረገ መሆኑ ታውቋል።

የቡሳ ጎኖፋ ኦሮሚያ ኃላፊ  ሙስጠፋ ከድር፤ በክልሉ ስምንት ዞኖች ለድርቅ አደጋ ተጋላጭ ለነበሩ 3 ነጥብ 2 ሚሊዮን ዜጎች ድጋፍ ሲደረግ መቆየቱን ተናግረዋል።

በተያዘው በጀት ዓመትም በተመሳሳይ ችግር ላይ ለሚገኙ 3 ነጥብ 7 ሚሊዮን ዜጎች ሰብአዊ ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

ከሐምሌ 1 ቀን 2014 ዓ.ም ጀምሮ  ከ300 ሺህ ኩንታል በላይ እህል በድርቅ ለተጎዱ ሰዎች ተደራሽ መደረጉን ጠቁመዋል።  

በ2014 በጀት ዓመት በስምንት ዞኖች ላይ ተከስቶ የነበረው የድርቅ ችግር አሁን ላይ ወደ አሥር ዞኖች መስፋፋቱን ጠቅሰው፤ ሰብአዊ ድጋፉም ተጠናክሮ መቀጠሉን ገልጸዋል።

በቦረና፣ ጉጂ፣ ባሌና ምስራቅ ባሌ፣ ምስራቅና ምዕራብ ሐረርጌ፣ አርሲ እና ምዕራብ አርሲ በስምንት ወረዳዎች ድርቁ መከሰቱን ተናግረዋል።

ለእነዚህ አካባቢዎችም ከ300 ሺህ ኩንታል በላይ ምግብና ምግብ-ነክ ድጋፎች መደረጋቸውን ጠቅሰዋል።

የምግብ እህል ማድረስ ባልተቻለባቸው አካባቢዎችም ገዝተው እንዲጠቀሙ የገንዘብ ድጋፍ መደረጉን አስታውሰዋል።

አሁን ላይ በድርቅ ለተጎዱ አካባቢዎች በአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን እና በክልሉ ቡሳ ጎኖፋ ድጋፍ ተደራሽ እየተደረገ መሆኑንም ተናግረዋል።  

የዝናብ ሁኔታ በቆላማ አካባቢዎች በሚፈለገው መልኩ ባለመዝነቡ የተዘራው እህል በመድረቁ የተረጂዎች ቁጥር ሊጨምር እንደሚችል ገልጸው፤ ድጋፍ የሚፈልጉ የተጨማሪ ሰዎች ብዛት ለማወቅ ጥናት እየተደረገ ይገኛል ብለዋል።

ከቦረና እስከ ምስራቅ ሐረርጌ ባሉት ቆላማ ዞኖች ዝናብ ማግኘት የሚጀምሩት ከነሐሴ መጨረሻ ጀምሮ በመሆኑ በአጭር ጊዜ የሚደርሱ ሰብሎችን እንዲዘሩ ከግብርና ቢሮ ጋር እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ከዚህም በተጨማሪ በክልሉ በስምጥ ሸለቆ አካባቢ የሚገኙ አሁን እየጣለ ባለው ዝናብ ቶሎ የሚደርሱ እህሎችን ከዘሩ ድርቁን ለተወሰኑ ወራት መቋቋም እንደሚችሉ ጠቁመዋል።

መንግሥት፣ ሕብረተሰቡና አጋር አካላት እስከ ሰኔ 30 ቀን 2014 ዓ.ም ድረስ 2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ኩንታል እህል ድጋፍ መደረጉንም አስታውሰዋል።

ከዚህም በተጨማሪ እህል ከገበያ ገዝቶ እንዲጠቀሙ ከ112 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ መደረጉን ተናግረዋል።

በድርቁ ምክንያት የሰው ሕይወት አልፏል በሚል በተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያዎች የሚገለጸው ወሬም ፍጹም እውነታ የሌለው መሆኑን ጠቅሰዋል።

ድርቅ በተከሰተባቸው ዞኖች የተወሰነ ዝናብ በመጣሉ ለእንስሳት የተሻለ ሁኔታ ቢፈጥርም ለእህል ምርት ግን በቂ ባለመሆኑ ድርቁ መቀጠሉን ገልጸዋል።

ከዚህም በተጨማሪ በአሸባሪው ሸኔ የተፈናቀሉትን ወደ ቀያቸው የመመለስና ድጋፍ የማድረግ ሥራ ተጠናክሮ መቀጠሉን ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም