በኦሮሚያ ክልል በግብርና ማቀነባበር ዘርፍ ለሚሰማሩ ባለሃብቶች አስፈላጊው ድጋፍ ይደረጋል- ርዕሰ መስተዳደር ሽመልስ አብዲሳ

86

ሐምሌ 30 ቀን 2014(ኢዜአ) በኦሮሚያ ክልል በግብርና ማቀነባበር ዘርፍ ለሚሰማሩ ባለሃብቶች አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደረግ የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር ሽመልስ አብዲሳ አስታወቁ።

የቡልቡላ የተቀናጀ ግብርና ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ ፓርክን የሚያስተዋውቅ መድረክ በአዲስ አበባ ተካሂዷል።

በመድረኩ ላይ የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ መላኩ አለበልን ጨምሮ የፌደራልና የክልል የሥራ ኃላፊዎች የተገኙ ሲሆን ፓርኩ በሚሰጣቸው አገልግሎቶች፣ ማበረታቻዎች እና ጠቀሜታዎች ላይ ማብራሪያ ተሰጥቷል።

የቡልቡላ ኢንዱስትሪ ፓርክ ባለሃብቶችን ለመቀበል አስፈላጊው ዝግጅት ያደረገ ሲሆን በከፍተኛ ወጪ ለግብርና ማቀነባበር የሚረዱ መሰረተ-ልማቶች ተሟልቶለታል ተብሏል።

ከ120 በላይ ባለሃብቶች ኢንቨስት ማድረግ የሚያስችል ሲሆን ለ100 ሺህ ሰዎችም የሥራ እድል መፍጠር እንደሚያስችል ነው በመድረኩ ላይ የተብራራው።

የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳደር ሽመልስ አብዲሳ እንዳሉት፤ በክልሉ ባለፉት ሦስት ዓመታት በሺዎች የሚቆጠሩ ባለሃብቶች ድጋፍ አግኝተው ወደ ኢንቨስትመንት እንዲገቡ ሁኔታዎች የማመቻቸት ሥራ ተካሂዷል።

የአርሶ አደሮችን ኢንቨስትመንት ማጠናከር ላይ ውጤታማ ተግባራት ተከናውኗል ያሉት ፕሬዝዳንቱ፤ አርሶ አደሮች በነጻ የሊዝ መሬት እንዲያገኙ የሚያደርግ አሰራር መዘርጋቱንም ተናግረዋል።

እስካሁን ባለው ሂደትም ወደ 9 ሺህ የሚጠጋ አርሶ አደር በዚህ አሰራር ተጠቃሚ ለማድረግ እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑንም አብራርተዋል።

ወጣቶች ከትንንሽ ኢንዱስትሪዎች ወደ ትልልቅ ኢንዱስትሪዎች እንዲሸጋገሩ ለማድረግም ድጋፎች እየተደረጉ እንደሆነም ነው የተናገሩት።

ክልሉ ኢንዱስትሪ ፓርኮችን ጨምሮ ግዙፍ የኢኮኖሚ ዞን ለመፍጠር እየተንቀሳቀሰ መሆኑን የገለጹት ፕሬዝዳንት ሽመልስ ባለሃብቶች መሰል እድሎችን በመጠቀም እንዲሰማሩ ነው ጥሪ ያቀረቡት።

የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ መላኩ አለበል በበኩላቸው፤ መንግሥት የአገሪቷን የኢኮኖሚ ሽግግር እውን ለማድረግ የግብርና ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ ፓርኮችን ወደ ሥራ እያስገባ ነው።

May be an image of 1 person

ባለፉት ሦስት ዓመታት ቡልቡላ፣ይርጋለምና የቡሬ የግብርና ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ ፓርኮች መገንባታቸውን የገለጹት ሚኒስትሩ ኢንቨስት የሚያደርጉ ባለሃብቶችም እየተመዘገቡ መሆኑን አንስተዋል።

እስካሁን በፓርኮቹ ውስጥ 94 ባለሃብቶች መመዝገባቸውን ጠቁመው፤ ከተመዘገቡት ውስጥ ስድስት ባለሃብቶች ማምረት መጀመራቸውን አስታውቀዋል።

በግብርና ማቀነባበሪያ ፓርኮቹ ውስጥ ተመዝግበው ሥራ ከመጀመሩ ባለሃብቶች ውስጥ ሦስቱ ወደ ውጭ መላክ የጀመሩ ሲሆን በሁለት ዓመት ውስጥ 16 ነጥብ 2 ሚሊዮን ዶላር ከውጭ ንግድ መገኘቱንም አክለዋል።

ኢንዱስትሪ ፓርኮቹ ሥራ መጀመራቸው 144 ሺህ አነስተኛ አርሶ አደሮች ምርታቸውን እንዲያቀርቡ ማስቻሉንም ተናግረዋል።

ግብርና ማቀነባበሪያዎቹ ሥራ መጀመራቸው ለቴክኖሎጂ ሽግግር፣ ለምርት ጥራት ማደግም ያለው ፋይዳ ከፍተኛ መሆኑን ነው ሚኒስትሩ የጠቀሱት።

ኢትዮጵያ ከግብርና የምታገኘው ገቢ ትልቁን ድርሻ የሚይዝ ቢሆንም እሴት የተጨመረባቸው አይደሉም ያሉት አቶ መላኩ የግብርና ፓርኮቹ ወደ ሥራ መግባት እሴት የታከለባቸውን ምርቶች ወደ ውጭ ለመላክ የሚያስችል መሆኑንም አክለዋል።

ግብርና ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ ፓርኮችን ለመገንባት 25 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ወጪ ተደርጓል ያሉት ሚኒስትሩ የቡልቡላ ግብርና ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ ፓርክ ብቻ 10 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር ፈጅቷል ብለዋል።

መንግሥት ከፍተኛ ወጪ በማውጣት ባለሀብቶች ላይ የሚፈጠረውን ጫና ለማቃለል እየሰራ ነው፤ ባለሃብቶችም እድሉን በመጠቀም ኢንቨስት ማድረግ እንደሚኖርባቸው አመልክተዋል።

May be an image of 1 person and text that says "etv"

የኦሮሚያ ኢንቨስትመንትና ኢንዱስትሪ ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ተሾመ አዱኛ እንደተናገሩት፤ የቡልቡላ ኢንዱስትሪ ፓርክ ለባሀብቶች ደረጃውን የጠበቀ አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ነው።

በኦሮሚያ ክልል ያለውን እምቅ የግብርና አቅም ለመጠቀም እየተሰራ መሆኑንም ነው የተናገሩት።