በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ከ1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ 38 ባለሀብቶች ወደ ስራ ገብተዋል

52

ሚዛን አማን፣ ሐምሌ 30 ቀን 2014 (ኢዜአ) በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ከ1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ 38 ባለሀብቶች በግብርና፣ በአገልግሎት ዘርፍና በሌሎች የኢንቨስትመንት አማራጮች ወደ ስራ እንዲገቡ መደረጉን የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ ተነገሩ።

ክልሉ ከተመሠረተበት ህዳር 2014 ዓ.ም ጀምሮ የልማት፣ የመልካም አስተዳደርና የፍትህ ጥያቄዎችን ለመመለስ ውጤት የታየበት ስራ ማከናወኑን ተናግረዋል።

ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ ክልሉ ከተመሰረተበት ጊዜ ጀምሮ በተከናወኑ ዋና ዋና ተግባራት ዙሪያ ዛሬ በሰጡት መግለጫ በሁሉም መስኮች መሻሻሎች መኖራቸውን ተናግረዋል።

የክልሉን ህዝብ የልማት፣ የመልካም አስተዳደርና የፍትህ ጥያቄዎችን ሊፈታ የሚያስችል ተቋም ማደራጀትና የሰው ሃይል ለማሟላት ጥረት መደረጉን ገልጸው፤ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች አስተያየት የተካተተበት የሰባት ወር ዕቅድ ተዘጋጅቶ ወደ ስራ መገባቱን አስታውሰዋል።

በግብርና ዘርፍ በበልግና በመኸር እርሻ 548 ሺህ ሄክታር መሬት በማልማት ከ55 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት መገኘቱን ገልጸው፤ ለቡና ምርት ልዩ ትኩረት በመስጠት ከ64 ሺህ 400 ቶን በላይ ቡና ለማዕከላዊ ገበያ ማቅረብ መቻሉን ጠቁመዋል።

በበጀት ዓመቱ ንቅናቄ በመፍጠር በ 7 ወራት 3 ቢሊየን 17 ሚሊየን ብር ገቢ መሰብሰቡን አስታውቀዋል።

በክልሉ ከ195 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች ቋሚና ጊዜያዊ የስራ ዕድል መፍጠር መቻሉንም ገልጸዋል።

የዋጋ ንረትና የኑሮ ውድነቱን ለማቃለል በማህበራት በኩል የተለያዩ የግብርና ምርቶችን የማቅረብና ህገ ወጥ የንግድ እንቅስቃሴን የመከላከል ስራ መሰራቱን ገልጸዋል።

ከ1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ 38 ባለሀብቶች በግብርና፣ በአገልግሎት ዘርፍና በሌሎች የኢንቨስትመንት አማራጮች ወደ ስራ እንዲገቡ መደረጉን አስታውቀዋል።

በጸጥታ ዘርፍ በድንበር አካባቢ አልፎ አልፎ የሚስተዋለውን የጸጥታ ስጋትና በአርብቶ አደሮች አካባቢ ከጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች ጋር በተያያዘ የሚከሰት ግጭትን ለመቆጣጠርና ለመከላከል ከህብረተሰቡ ጋር በመወያየት የተሰራው ስራ አንጻራዊ ሰላም ማምጣት ማስቻሉን አስረድተዋል።

ወደ ጫካ ሸፍተው የገቡ ግለሰቦች እጃቸውን ለመንግስት መስጠታቸውን ጠቅሰው፤ ቀላል ጥፋት ያጠፉት ማህበረሰቡ ምህረት አደርጎላቸው ሰላም መፍጠር እንደተቻለ አስረድተው፤ የጸጥታ ስጋቶችን  ሙሉ በሙሉ ለመፍታት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ክልሉ ሲመሰረት በህዝቦች መፈቃቀድና መከባበር ብዝሃ ዋና ከተሞች እንዲኖሩት መደረጉን አመልክተው፤ ከክልሉ ነዋሪ ጋር በመመካከርና በህገ መንግስቱ በማስቀመጥ  የፖለቲካና የአስተዳር ዘርፍ በቦንጋ ማዕከል እንዲሆን መወሰኑን ገልጸዋል።

የህግ አውጪውን በተርጫ ማዕከል፣ የዳኝነት አካሉን በሚዛን አማንና የብሔረሰቦች ምክር ቤት በቴፒ ከተማ በማድረግ ክልሉ 4 ብዝሃ ከተሞች እንዲኖሩት ተወስኖ ወደ ስራ መገባት መቻሉን ተናግረዋል።

በብዝሃ ዋና ከተማነት ከተለዩት ከተሞች ውጭ የአመያና የጀሙ ከተሞችም ተያይዞ ለማደግና ለመልማት በተቀመጠው መርህ መሰረት ከተጠሪ ተቋማት ድልድል ተደራሽ እንደሚደረጉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ ገልጸዋል።

ብዝሃ ከተሞች መኖራቸው እርስ በርስ እንዲተሳሰሩ፣ እንዲረዳዱና ባህላቸውን እንዲለዋወጡ የሚረዳ መሆኑን ገልጸዋል።