ሕብረተሰቡ አቅሙ በፈቀደ መጠን የአዕምሮ ዕድገት ውስንነት ያለባቸውን ዜጎች ሊደግፍ ይገባል -ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው

ሐምሌ 30 ቀን 2014(ኢዜአ) ሕብረተሰቡ አቅሙ በፈቀደ መጠን የአዕምሮ ውስንነት ያለባቸውን ዜጎች እንዲደግፍ ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው ጥሪ አቀረቡ።

የቀዳማዊት እመቤት ጽህፈት ቤት በለገጣፎ የፋውንዴሽኑ ቅጥር ግቢ ውስጥ ያስገነባውን ትምህርት ቤት ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው መርቀው ሥራ አስጀምረዋል።

ትምህርት ቤቱን ገንብቶ ለማጠናቀቅ 19 ሚሊየን ብር ወጪ የተደረገ ሲሆን ግንባታውም ከአንድ ዓመት ባነሰ ጊዜ ውስጥ የተጠናቀቀ ነው ተብሏል።

የግንባታው ወጪ በቀዳማዊት እመቤት ጽህፈት ቤት የተሸፈነ ሲሆን፤ ከቀጣይ ዓመት ጀምሮ 300 የሚሆኑ የአዕምሮ ዕድገት ውስንነት ያለባቸውን ተማሪዎችን ተቀብሎ ያስተምራል ነው የተባለው።

ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው ትምህርት ቤቱን መርቀው በከፈቱበት ወቅት እንዳሉት፤ በኢትዮጵያ እንደዚህ አይነት መረዳዳቶች ሊዳብሩ ይገባል።

"በማኅበሰረቡ ዘንድ የአዕምሮ ዕድገት ውስንነት ባለባቸው ዜጎች ላይ ያለው አስተሳሰብ መለወጥ አለበት" ሲሉ አስገንዝበዋል።

ሕብረተሰቡ የአዕምሮ ዕድገት ውስንነት ያለባቸው ሰዎችን በማበረታታት ከጎናቸው ሆኖ እንዲያግዛቸውም ጥሪ አቅርበዋል።

የዲቦራ ፋውንዴሽን መሥራች አባዱላ ገመዳ በበኩላቸው፤ የቀዳማዊት እመቤት ጽህፈት ቤት በቅጥር ግቢው ላስገነባው ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ምስጋና አቅርበዋል።

May be an image of 1 person

በቅጥር ግቢው ከመዋዕለ-ህፃናት ጀምሮ የመጀመሪያ ደረጃ እንዲሁም ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል እየተገነባ መሆኑን ጠቁመው ግንባታዎቹ እስከ ጥቅምት 2015 ዓ.ም ተጠናቆ ወደ ሥራ እንደሚገቡ ተናግረዋል።

ከሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር የሥርዓተ-ትምህርት ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ገልጸው፤ በሦስት ዩኒቨርሲቲዎች በተቋሙ የሚሰሩ ባለሙያዎች ሥልጠና እየወሰዱ መሆኑን ጠቁመዋል።

የአዕምሮ ዕድገት ውስንነት ያለባቸው ህፃናት አስፈላጊው ድጋፍ እስከተደረገላቸው ድረስ ሌሎች ሰዎች የሚደርሱበት ቦታ ላይ እንደሚደርሱም አቶ አባዱላ ገልጸዋል።

የኦሮሚያ ትምህርት ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ገላና ወልደሚካኤል የማዕከሉ መቋቋም የበርካታ ሰዎችን ችግር ለመፍታት ያግዛል ብለዋል።

May be an image of 1 person and standing

በማኔጅመንት በኩል ለማዕከሉ 1 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር ድጋፍ እንዲደረግ መወሰኑንም ተናግረዋል።

እንዲሁም ቢሮው ቤተ-መጽሐፍቱን ለማሟላት ኃላፊነት ወስዶ እየሰራ መሆኑን ገልጸው፤ በቀጣይም ለተቋሙ አስፈላጊውን እገዛ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል።

የቀዳማዊት እመቤት ጽህፈት ቤት ይህንን ትምህርት ቤት ጨምሮ 24 ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን አስገንብቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም