በደባርቅ መጠለያ ለሚገኙ ወገኖች 3 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር የሚያወጣ የአልባሳት ድጋፍ ተደረገ

61

ጎንደር (ኢዜአ) ሐምሌ 30/2014–በህወሓት የሽብር ቡድን ወረራ ተፈናቅለው በደባርቅ መጠለያ ለሚገኙ ወገኖች 3 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር የሚያወጣ የአልባሳት ድጋፍ ተደረገ።

ለተፈናቀሉት ወገኖች ዛሬ ድጋፉን ያደረጉት በአሜሪካ ካሊፎርኒያ ግዛት የሚገኙ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ሊቃነ-ጳጳሳት ናቸው።

የሰሜን አሜሪካ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ፀሐፊና የሲኖዶሱ አባል ዶክተር አቡነ ጴጥሮስ ዛሬ ድጋፉን ሲያስረክቡ እንዳሉት፣ ቤተ-ክርስቲያኑዋ ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ ወገኖችን በመደገፍ የበኩሏን ትወጣለች።

“ሰላም ለሰው ልጆች የህልውና መሰረት በመሆኑ ስለሰላም አጥብቀን እንጸልይ፤ ሰላም እንዲወርድም ቤተክርስቲያኗ ትሰራለች” ብለዋል።

የተፈናቀሉ ወገኖችን አቅም በፈቀደ መጠን መደገፍ እንደሚገባ የገለጹት ዶክተር አቡነ ጴጥሮስ፣ ለዚህም በአሜሪካ ደቡብ ካሊፎርንያ ግዛት የሚገኙ ሊቃነ-ጳጳሳት ባሰባሰቡት ገንዘብ 710 ካርቶን የሴቶችና የህጻናት አልባሳት ዛሬ ድጋፍ ማድረጋቸውን ገልፀዋል።

ድጋፉን የተረከቡት የሰሜን ጎንደር ዞን ምግብ ዋስትናና አደጋ መከላከል ተጠሪ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ሰላምይሁን ሙላት በበኩላቸው፣ በሕወሓት የሽብር ቡድን ወረራ በርካታ ሰዎች መፈናቀላቸውን ገልጸዋል።  

ከቄያቸው ተፈናቅለው በአሁኑ ወቅት በደባርቅ ጊዚያዊ መጠለያና በዘመድ ተጠልለው የሚገኙ ከ142ሺህ በላይ ዜጎች መኖራቸውንም አስረድተዋል።

የቤተ-ክርስቲያኑዋ ሊቃነ-ጳጳሳት ዛሬ ያደረጉት የአልባሳት ድጋፍ ወቅቱ ክረምት በመሆኑ ተፈናቃይ ወገኖችን ከብርድ ለመታደግ እንደሚያስችል ገልጸዋል።

በተመሳሳይ በሰሜን አሜሪካ የሚገኙ የአዲአርቃይና አካባቢው ተወላጆች በህወሓት የሽብር ቡድን ወረራ ተፈናቅለው በደባርቅ ቁልጭ ሜዳ መጠለያ ጣቢያ ለሚገኙ ተፈናቃይ ወገኖች ግምቱ 420 ሺህ ብር የሆነ የምግብ ድጋፍ አድርገዋል።

የተወላጆቹ ተወካይ አቶ ሙሉቀን አዛናው እንደተናገሩት ድጋፉ 100 ኩንታል የጤፍ ዱቄት እና 20 የስፖንጅ ፍራሾች ናቸው።

ድጋፉ ከተደረገላቸው ተፈናቃይ ወገኖች መካከል ወይዘሮ አበባ ደምሌ እንዳሉት፤ መንግስት፣ ግብረ ሰናይ ድርጅቶችና በጎ አድራጊ ግለሰቦች የእለት ደራሽ ምግቦችን በማቅረብ እየደገፏቸው ይገኛሉ።

“ድጋፉ ለችግራችን የደረሰ ነው። ለተደረገልን መልካም ተግባር ምስጋናዬ ከፍያ ያለ ነው” ያሉት ደግሞ ከአዲአርቃይ ወረዳ ተፈናቅለው በደባርቅ ጊዚያዊ መጠለያ የሚገኙት ወይዘሮ አቅልነሽ ጥጋቡ ናቸው።

በአሸባሪው ህወሓት ከቄያቸው ተፈናቅለው በተለያዩ አካባቢዎች ለሚገኙ ወገኖች መንግስት፣ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ ዳያስፖራዎች እንዲሁም ባለሃብቶች ድጋፍ እያደረጉ መሆኑ ይታወቃል።