በአማራ ክልል ከ143 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተገነቡ የባዮ ጋዝ ማብላያ ጣቢያዎች ለአገልግሎት በቅተዋል

238

ባህር ዳር ፣ ሐምሌ 30 ቀን 2014 (ኢዜአ) በአማራ ክልል በ2014 ዓ.ም በጀት ዓመት ከሁለት ሺህ በላይ የባዮ ጋዝ ማብላያ ጣቢያዎች ከ143 ሚሊዮን ብር በሆነ ወጪ ተገንብተው ለአገልግሎት መብቃታቸውን የክልሉ የውሃና ኢነርጂ ቢሮ አስታወቀ።

ቢሮው ከ167 ሺህ በላይ ማገዶ ቆጣቢ ምድጃዎችን ማሰራጨቱን ገልጿል።

የአማራ ክልል ውሃና ኢነርጂ ቢሮ የባዮ ኢነርጂ ምንጮችና ቴክኖሎጂዎች ልማት ማስፋፊያ ዳይሬክተር አቶ ወንድም በሪሁን በተጠናቀቀው በጀት ዓመት 1 ሺህ 498 የባዮ ጋዝ ማብላያ ጣቢያዎችን ለመገንባት ታቅዶ 2ሺህ 375 መገንባቱን ለኢዜአ ገልጸዋል።

ለጣቢያዎቹ ግንባታ 143 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ወጪ እንደተደረገባቸው ጠቁመዋል።

May be an image of 2 people and outdoors

በተጨማሪም ከ174 ሺህ በላይ የተለያዩ ማገዶ ቆጣቢ ምድጃዎችን አዘጋጅቶ ለማሰራጨት ታስቦ 167 ሺህ 400 ምድጃዎችን ለዜጎች ተደራሽ ማድረግ መቻሉን አመልክተዋል።

የባዮ ጋዝ ማብላያ ጣቢያዎቹና ምድጃዎቹ የዜጎችን የጤና፣ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ለመፍታት አስተዋጽኦ እንዳላቸው ነው አቶ ወንድም ያስረዱት።

በ2015 ዓ.ም በጀት ዓመትም የባዮ ጋዝ ቴክኖሎጂን በማስፋፋትና ማገዶ ቆጣቢ ምድጃዎችን በማሰራጨት የአርሶ አደሩን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ይበልጥ ለማቃለል በትኩረት ይሰራል ብለዋል።

የባዮ ጋዝ ማብላያ ጣቢያ እና የምድጃ ተጠቃሚ አርሶ አደሮች በበኩላቸው ከምግብ ማብሰያነት ባለፈ ኃይል አመንጭቶ የሚወጣውን ዝቃጭ ለእርሻ ሥራቸው እንደ ማዳበሪያነት እየተጠቀሙበት መሆኑን ገልጸዋል።

የባዮጋዝ ቴክኖሎጂ የሚያስገኘው ጥቅም ዘርፈ ብዙ ነው፤በተለይም ጭስ በዓይን ላይ ያስከትል የነበረውን የጤና ችግር አስቀርቶልናል ብለዋል።

በአማራ ክልል በተጠናቀቀው በጀት አመት የተገነቡትን ጨምሮ 15 ሺህ 341 የባዮ ጋዝ ማብላያ ጣቢያዎች አገልግሎት እየሰጡ እንደሚገኝ ከክልሉ ውሃና ኢነርጂ ቢሮ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ