የጸጥታ ኃይሉ በወሰደው እርምጃ 24 የአልሸባብ አመራሮችን ጨምሮ ከ800 በላይ የቡድኑ ተዋጊዎች ተደምስሰዋል

155

ሐምሌ 29 ቀን 2014 (ኢዜአ) የጸጥታ ኃይሉ በወሰደው እርምጃ እስካሁን ባለው ሂደት 24 የአልሸባብ አመራሮችን ጨምሮ ከ800 በላይ የሽብር ቡድኑ ተዋጊዎች መደምሰሳቸውን ጊዜያዊ የጸጥታ ኮማንድ ፖስት አስታወቀ፡፡

ድሽቃን ጨምሮ በርካታ የቡድንና የነፍስ ወከፍ መሳሪያዎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውም ነው የተገለጸው፡፡

የመከላከያ ኃይል ስምሪት ኃላፊና የጊዜያዊ ኮማንድ ፖስቱ አስተባባሪ ሜጀር ጄነራል ተስፋዬ አያሌው እና የሶማሌ ክልል ልዩ ኃይል አዛዥ ኮሚሽነር ጄነራል መሃመድ አህመድ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ የአልሸባብ የሽብር ቡድን ከሐምሌ 14 ቀን 2014 ዓ.ም ጀምሮ ወደ ኢትዮጵያ ሰርጎ ለመግባት ያደረገው ሙከራ በፀጥታ ኃይሉና በሕዝቡ የተቀናጀ እርምጃ ሙሉ በሙሉ ከሽፏል።

ሜጀር ጄነራል ተስፋዬ እንደሚሉት፤ ኢትዮጵያን ለማተራመስ የሚሹ የውጭ ጠላቶች የውስጥ ባንዳዎችን በመቅጠር ከፍተኛ ጥረት ሲያደርጉ ቆይተዋል፡፡

እቅዳቸው እንዳሰቡት አልሳካ ሲላቸው በአሁኑ ወቅት አልሸባብን ከኋላ በመደገፍ ከንቱ ሙከራ ማድረጋቸውንም ነው ያብራሩት፡፡

ይህም ኢትዮጵያ የተፈጥሮ ጸጋዎችን ተጠቅማ ለመልማት የጀመረችውን ተስፋ ሰጪ ሥራ ለማደናቀፍ ያለመ ሙከራ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

በዚህም አልሸባብ ኢትዮጵያና ሶማሊያ በሚዋሰኑባቸው አካባቢዎች የተወሰነ ኃይሉን በ16 ተሽከርካሪዎች በመጫንና የተወሰነውን ደግሞ ጨለማን ተገን አድርጎ በእግር ወደ ኢትዮጵያ ሰርጎ በማስገባት ጥቃት ለመፈጸም መሞከሩን ነው የገለጹት፡፡

ነገር ግን የመከላከያ ሰራዊቱ ከሶማሌ ክልል ልዩ ኃይል ጋር በመቀናጀት በወሰደው እርምጃ ወደ ኢትዮጵያ ሰርጎ ለመግባት የሞከሩ የሽብር ቡድኑ አመራሮችን ጨምሮ ተዋጊዎቹ ሙሉ ለሙሉ ተደምስሰዋል ነው ያሉት፡፡

የኢፌዲሪ አየር ኃይል የተመረጡ ኢላማዎችን ነጥሎ በመምታት የሽብር ቡድኑ ለረዥም ጊዜ እጠቀምበታለሁ ብሎ ያዘጋጀውን የሎጂስቲክስና ጦር መሳሪያ ክምችት ያወደመ ሲሆን፤ የሽብር ቡድኑን አመራሮችም መደምሰስ ችሏል፡፡

በዚህም የሚከተሉት የሽብር ቡድኑ አመራሮች መደምሰሳቸው ተገልጿል:-

1) ፉአድ መሐመድ ከሊፍ -የአልሸባብ ቅስቀሳና ፕሮፓጋንዳ ኃላፊ

2) አብዱልአዚዝ አቡሙስ -የአልሸባብ ቃል አቀባይ

3) አብዲኑር ኢሴ -የቦኮል ዞንና የኢትዮጵያ ድንበር አዋሳኝ ኃላፊ

4) ሸክ ለአብ ሶማሊያዊ -የደቡብ ምስራቅ ሎጂስቲክ ኃላፊ

5) አቡ ሙሳ - ምክትል አፈጉባኤ

6) አሊ መሃመድ ሃሰን - የአልሸባብ ማዕከላዊ ኮሚቴ አማኒያት ሁለተኛ ሰው

7) አደም -ወደ አገር ውስጥ ሰርጎ ለመግባት የሞከረው የሽብር ቡድኑ ምክትል አዛዥ

8) ሙክታር ጋብ - ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል

9) አሚር አብደላ (መሃመድ አብዱላሂ) - ሞርጋቤ ካምፕ የአልሸባብ ስልጠና ኃላፊ

10) ኢንጂነር ጀሃድ ስሬዋን (ሙጃሂድ ፈይሰል) - በብሉፍላይ ካምፕ የማሠልጠኛ ኃላፊና የፈንጅ ኃላፊ

11) ሼክ ሁሴን በርደሌ - የባይና ቦከል ዞን ቀረጥ ሰብሳቢ

12) ሼክ ሃሰን ኑኖ -የታችኛው ሸበሌ ጀበሃ ዘመቻ ኃላፊ

13) ያሲን ደሬ - አሚር

14) ሳላህ ደሬ - የባይ ዞን የአልሸባብ ትምህርት ኃላፊ

15) አቡሠላም - የቦኮል ዞን የአልሸባብ ሰብሳቢ

16) ሃምዚ አቡዱላሂ - የባይ ዞን መረጃ ኃላፊ

17) አብዱላሂ ሃጅ - የባይና ቦኮል ዞን ወታደራዊ አዛዥ

18) ሙክታር ቦሮ - አሚር

19) አብዱረሽድ ጋቦ- አሚር

20) አብዱኪም ገዱደ- አሚር

21) ሙክታር ጋብ - የቀጣና ዘመቻ ኃላፊ

22) አዩብ ዳውድ - አሚር

23) አሊ አደን---አሚር

24) ሃሰን መሃመድ--አሚር ናቸው።

እንደ ሜጀር ጄነራል ተስፋዬ ገለጻ፤ የጸጥታ ኃይሉ ያከናወነው ኦፕሬሽን የመከላከያ ሠራዊት፣ የአየር ኃይል እንዲሁም የሶማሌ ክልል ልዩ ኃይልና ሕዝብ ጀግነነትን በተግባር ያረጋገጠና ኢትዮጵያን ለመድፈር የሚሞክሩ ኃይሎች ደጋግመው ማሰብ እንዳለባቸው ትምህርት የሰጠ ነው፡፡

የክልሉ ነዋሪዎች የጸጥታ ኃይሉን ደጀን ሆነው በመደገፍ ረገድ አኩሪ ተግባር ማከናወናቸውንም አብራርተዋል፡፡

አሁን ላይ የሽብር ቡድኑ በውስጥ ያዘጋጃቸው ሴሎችን የማጥራት ሥራ እየተከናወነ መሆኑንም  ነው የገለጹት፡፡

የሶማሌ ክልል ልዩ ኃይል አዛዥ ኮሚሽነር ጄነራል መሐመድ አህመድ የሽብር ቡድኑ አቶ፣ የድ፣ ኤልበርዴና ወሻ በተባሉ የጠረፍ አካባቢዎች ጥቃት ለመፈጸም መሞከሩን ተናግረዋል።

በወቅቱ የመከላከያ ሰራዊቱና ሶማሌ ክልል ልዩ ኃይል በጀግንነት በመዋጋት የኢትዮጵያ አለኝታነታቸውን በተግባር አሳይተዋል ነው ያሉት፡፡

በዚህም የአልሸባብ 24 ቁንጮ አመራሮችን ጨምሮ 813 የሽብር ቡድኑ ተዋጊዎች መደምሰሳቸውን ጠቅሰው፤ አልሸባብ በዚህን ያህል ቁጥር በአንድ ጊዜ ኮር አመራሮቹ ሲገደሉበት ይህ የመጀመሪያ ጊዜ ሊሆን እንደሚችልም ነው የጠቆሙት፡፡

የሽብር ቡድኑ ተዋጊዎቹን ወደ ኢትዮጵያ አስርጎ ለማስገባት የተጠቀመባቸው ተሽከርካሪዎችን ጨምሮ በርካታ የጦር መሳሪያዎች መውደማቸውንም ተናግረዋል፡፡

ድሽቃን ጨምሮ በርካታ የቡድንና የነፍስ ወከፍ መሳሪያዎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውንም እንዲሁ፡፡

አጠቃላይ በኦፕሬሽኑ የሶማሌ ክልል ሕዝቦች የየትኛውም የጥፋት ቡድን ተባባሪ አለመሆናቸውን በተግባር ያሳዩበትና የጸጥታ ኃይሉም አገሩን ለመጠበቅ ሁሌም ዝግጁ መሆኑ በተግባር ያረጋገጠበት መሆኑንም በአጽንኦት ተናግረዋል፡፡ 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም