ዩኒቨርሲቲው ችግር ፈች ጥናትና ምርምር ላይ በትኩረት ሊሰራ ይገባል- አቶ ሞገስ ባልቻ

136

መቱ ሐምሌ 29/2014 (ኢዜአ) መቱ ዩኒቨርሲቲ በሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎችና ህዝቦች ዘንድ ጎልቶ እንዲወጣ ችግር ፈቺና ተግባራዊ መሆን የሚችሉ የጥናትና ምርምር ስራዎችን በትኩረት መስራት እንደሚገባው የዩኒቨርሲቲው የስራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ሞገስ ባልቻ አስገነዘቡ።

ዩኒቨርሲቲው አስረኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን እያከበረ ነው።

በጠቅላይ ሚኒስቴር ጽሕፈት ቤት የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማዕከል የዘርፍ አስተባባሪ ሚኒስትርና የዩኒቨርሲቲው የስራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ሞገስ ባልቻን ጨምሮ የቀድሞ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንቶች፣ የስራ አመራር ቦርድ አባላትና የዞኑ አመራሮች በበዓሉ ላይ ተገኝተዋል።

የእለቱ የክብር እንግዳና የዩኒቨርሲቲው የስራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ሞገስ ባልቻ እንደገለፁት ዩኒቨርሲቲው ትልቅ አቅም ያለው በመሆኑ በሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎችና ሕዝቦች ዘንድ ጎልቶ እንዲታወቅ ችግር ፈቺና ተግባራዊ መሆን የሚችሉ የጥናትና ምርምር ስራዎች ላይ ትኩረት ሰጥቶ ሊሰራ ይገባል።

ዩኒቨርሲቲው ትልቅ አቅም እያላቸው በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እጥረት የተለያዩ የትምህርት ዕድሎች ተጠቃሚ ያልነበሩን የአካባቢውን ነዋሪዎች ችግር የቀረፈ መሆኑን ተናግረዋል።

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር እንደገና አበበ በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው የተደራጀ ቤተ መጽሀፍትም ሆነ የመለማመጃ ቤተ ሙከራ ባልነበረበት የዛሬ አስር ዓመት የመማር ማስተማር ስራውን እንደጀመረ ተናግረዋል።

ዩኒቨርሲቲው ባለፉት አስር ዓመታት ብዙ ውጣ ውረዶችን አልፎ ከ16 ሺህ በላይ ተማሪዎችን በአንደኛና በሁለተኛ ዲግሪ አስመርቆ ለዛሬ በዓል መድረሱን ገልፀዋል።

በዓሉ ዛሬን ጨምሮ ለሁለት ቀናት እንደሚከበርና  በዩኒቨርሲቲው ያለፉት አስር ዓመታት መልካም ክንውኖችና ሊሻሻሉ በሚገባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ምክክር እንደሚደረግ ተመላክቷል ።

የዩኒቨርሲቲው የወደፊት የትኩረት አቅጣጫዎች፣ ያለውን ምቹ ሁኔታና የተፈጥሮ ሀብት ተጠቅሞ መስራት በሚችልባቸው አቅጣጫዎች ላይ ምክክሩ እንደሚያተኩር ተነግራል።

በ2004 ዓ.ም 300 ተማሪዎችን ተቀብሎ የመማር ማስተማር ስራውን የጀመረው መቱ ዩኒቨርሲቲ ዛሬ  በሰባት ኮሌጆችና በሁለት ትምህርት ቤቶቹ ከ26 ሺህ በላይ ተማሪዎችን በአንደኛና በሁለተኛ ዲግሪ በማስተማር ላይ እንደሚገኝ ከዩኒቨርሲቲው የተገኘው መረጃ ያመለክታል።  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም