ሃዋሳ የኒቨርሲቲ ከ13 ሺህ በላይ የፍራፍሬና ሀገር በቀል ችግኞችን ተከለ

297

ሀዋሳ ሐምሌ 29/2014 (ኢዜአ) የሃዋሳ የኒቨርሲቲ ማህበረሰብ አባላት ከ13 ሺህ በላይ የፍራፍሬና ሀገር በቀል ችግኞችን በዩኒቨርሲቲው ቅጥር ግቢ በመትከል አረንጓዴ አሻራቸውን አሳረፉ።

በችግኝ ተከላ መርሃግብሩ ላይ የተገኙት የዩኒቨርሲው ፕሬዚዳንት ዶክተር አያኖ በራሶ፤ አቮካዶ፣ ፓፓዬ፣ ማንጎና መሰል የፍራፍሬና ሀገር በቀል የዛፍ ችግኞችን በብዛት በማፍላት በተቋሙ ዋና ግቢና ሌሎች ግቢዎች የመትከል ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።

እንደ ሀገር አረንጓዴ ኢኮኖሚንና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚደረገውን ጥረት ለማገዝ ዩኒቨርሲቲው  የበኩሉን እየተወጣ መሆኑንም ገልፀዋል።

ዶክተር አያኖ እንዳሉት ዩኒቨርሲቲው በወንዶ ገነትና ሌሎች ካምፓሶቹ ውስጥ ባሉ የችግኝ ማፍያ ጣቢያዎች ከ1 ሚሊዮን በላይ ችግኞችን አፍልቷል።

በራሱ ከሚተክላቸው ችግኞች በተጨማሪ ለሲዳማ ክልል፣ ለምዕራብ አርሲ ዞንና በአካባቢው ለሚገኙ የማህበረሰብ ክፍሎች ከ300 ሺህ በላይ ችግኞችን ማሰራጨቱንም ተናግረዋል።

የሃዋሳ ሐይቅን ከደለል ለመከላከል የኒቨርሲቲው እያከናወነ ባለው ተግባርም በሐይቁ ዙሪያ ባሉ ወረዳዎች ከ100 ሺህ በላይ ችግኝ እንዲተከል መደረጉን ዶክተር አያኖ አመልክተዋል።  

የፍራፍሬና ሀገር በቀል የዛፍ ችግኝ ተከላ መርሀ-ግብሩ በሁሉም የዩኒቨርሲቲው ካምፓሶች ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ነው ፕሬዚዳንቱ ያመለከቱት።

የዩኒቨርሲቲው የማህበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክተር አቶ ማርቆስ ፍስሀ በበኩላቸው፣ በዘንድሮ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በዋናው ካምፓስ ብቻ 23ሺህ ችግኞችን ለመትከል መታቀዱን ገልጸዋል።

ከሚተከሉት ችግኞች መካከል 3ሺህ የሚሆኑት የፍራፍሬ ችግኞች ቀሪዎቹ ሀገር በቀል የደን ዛፍ ችግኞች መሆናቸውን ጠቁመዋል።

በዛሬው ዕለትም 13ሺህ የፍራፍሬና የደን ዛፍ ችግኞች መተከላቸውን አስረድተዋል።

ከዚህ ባሻገር የተራቆተ መሬት ባሉባቸው የአካባቢው ወረዳዎች 580ሺህ የተለያየ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞችን ለመትከል ታቅዶ እስካሁን ድረስ 460ሺህ መተከሉን አቶ ማርቆስ አስታውሰዋል።

በተከላው ከተሳተፉ የሃዋሳ ዩኒቨርሲቲው የማህበረሰብ አባላት መካከል የጥራት ማረጋገጥና ማሻሻል ዳይሬክቶሬት ተባባሪ ዳይሬክተር ቸሩ አፅመጊዮርጊስ እንደሀገር የተጀመረው የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር የኢትዮጵያን የደን ሽፋን ከማሳደግ ባለፈ በቀጠናው ሀገራት ላይ መነሳሳትን በመፍጠር በጎ ተፅዕኖ ያሳድራል።

በዓለም አቀፍ ደረጃ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል በሚደረገው ጥረት ኢትዮጵያ ቀዳሚ ሆና መልካም ገጽታን እንድትገነባ የሚያደርግ መሆኑን ተናግረዋል።

በመሆኑም የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ አባላት ችግኞችን ከመትከል ባለፈ ተገቢ እንክብካቤና ጥበቃ ማድረግ እንደሚገባም አሳስበዋል።

በዛሬው የችግኝ ተከላ መርሃ ግብሩ ላይ የዩኒቨርሲቲው አመራሮች፣ የአስተዳደር ሠራተኞች፣ መምህራንና ሌሎች የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ አካላት ተሳትፈዋል።