የቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ ጋምቤላና ኦሮሚያ ክልሎች የጋራ መድረክ በአሶሳ ተጀመረ

89

አሶሳ ፤ ሐምሌ 29 ቀን 2014 ዓ.ም (ኢዜአ) የቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ ጋምቤላና ኦሮሚያ ክልል ህዝቦች የጋራ የሰላምና ልማት ውይይት ዛሬ በአሶሳ ከተማ ተጀምሯል።

የሶስቱ ክልሎች የጋራ የሰላምና የልማት ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ፍሮምሳ ሰለሞን በወቅቱ እንዳሉት ክልሎቹ ህዝቦቻቸውን ተጠቃሚ ያደረጉ የልማት ስራዎች እያከናወኑ ይገኛሉ።

በክልሎቹ አጎራባች አካባቢዎች የሚገነቡ የመንገድ፣ ትምህርት ቤት፣ የውሃ ተቋማት እንዲሁም ሌሎች የመሰረተ ልማት ተቋማት ግንባታ ዋነኞቹ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

በተጨማሪም በግጭት ምክንያት ከቄያቸው የተፈናቀሉ ወገኖችን መልሶ ማቋቋም በሶስቱም ክልሎች በጋራ ከሚሰሩ ስራዎች መካከል እንደሚገኝበትም አንስተዋል።

በዛሬው እለት የተጀመረው የጋራ የምክክር መድረክም የተጀመሩ ስራዎችን አጠናክሮ ለማስቀጠል እና ቀጣይ አቅጣጫዎችን ለማሰቀመጥ ያለመ እንደሆነ ሃላፊው ተናግረዋል።

ሶስቱም ክልሎች እየተጠናከረ የመጣውን ግንኙነታቸውን ተጠቅመው የታላቁን የህዳሴ ግድብ አካባቢ ሰላም ለማጠናከር እንዲሰሩ ያስገነዘቡት ደግሞ የቤኒሻንጉል ጉሙዝና ኦሮሚያ ክልሎች የጋራ ሰላምና ልማት ማስተባበሪያ ጸህፈት ቤት አስተባባሪ አቶ ዲንሳ በየነ ናቸው።

ከሶስቱም ክልሎች የተውጣጡ ወደ አንድ ሺህ የሚጠጉ ነዋሪዎች እየተሳተፉበት የሚገኘው መድረክ እስከ ነገ እንደሚቀጥል ከመድረኩ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም